የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ የአየርላንድ አምሳደር ብሬናን ኒኮላን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ የአየርላንድ አምባሳደር የሆኑትን አምባሳደር ብሬናን ኒኮላን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ ከአንባሳደር ብሬናን ጋር ባደረጉት ቆይታ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅተቶች ባለስልጣን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ እንዲጎለብት ያደረጋቸውን መጠነ ሰፊ ስራዎችን በሚመለከት ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡
የአየርላንድ መንግስት በሲቪል ማህበረሰብ ድጋፍ ፕሮግራም ሁለት በ(CSSPII) በኩል ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ እየደገፈ እንደሚገኝና ይህም ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱም ሆነ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ትልቅ እገዛ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተው ለዚህም የአየርላንድ መንግስት አስተዋጽዖ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራባቸውን የምዕራፍ ሁለት ተቋማዊ የለውጥ አጀንዳዎችን የገለጹ ሲሆን በተለይም ስኬታማ ስራዎችን ማጽናት፣ ማላቅና ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ ማድረግ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡አያይዘውም በተቋሙ የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ በአመራር ደረጃ ያላቸውን ተሳትፎ ሃምሳ ከመቶ ለማድረስ በትጋት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው የአየርላንድ መንግስትም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአየርላንድ አምባሳደር ብሬናን ኒኮላን በበኩላቸው የአየርላንድ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር የዲፐሎማሲ ግንኙነት ከጀመረ 30 ዓመታት እንዳስቆጠረ አንስተው በሰብዓዊ መብት፣ በሰላም ግንባታ እና በሴቶች መብት ላይ እንዲሁም ከሀገራዊ ምክክር ጋር በተያያዘ በርካታ ስራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡
አዲሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ከወጣ በኋላ ዘርፉ ትልቅ መነቃቃትን እያሳየ እንደሚገኝ ያነሱት አምባሳደሯ ከበርካታ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋርም በቅርበት እየሰሩ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡