የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከግብር ነጻ አገልግሎት ስለሚያገኙበት ሁኔታ የተደረገ ውይይት

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከግብር ነጻ አገልግሎት ስለሚያገኙበት ሁኔታ ውይይት ተደረገ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጋር በመተባበር የተለያዩ የመንግስት ተቋማት ተወካዮችና የሲቪለ ማህበረሰብ ድርጅቶች ኃላፊዎች በተገኙበት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከታክስ ነጻ አገልግሎት ማግኘት ስለሚችሉበት ሁኔታ ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጀቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦን ጨምሮ በገንዘብ ሚንስቴር የፊሲካልና ፖሊሲ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙላይ ወልዱ ተገኝተዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ድርጅቶች ዓላማቸውን ሳይስቱ የህብረተሰብን ጥቅም ማዕከል አድርገው እንዲሰሩ ሁለት መስረታዊ የሆኑ የክትትልና የድጋፍ ሥርዓቶች እንዳሉ አንስተው አንደኛው በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ወይም በመንግስት በኩል የሚደረግ መንግስታዊ የክትትልና የድጋፍ ሥርዓት ሲሆን ሌላኛው በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በኩል የሚደረግ የርስ በርስ የቁጥጥርና የድጋፍ ሥርዓት ነው ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡
ሁለቱም የክትትልና የድጋፍ ሥርዓት ዋንኛ ዓላማ ማህበራዊ መስረት ያለው፤ በነጻነት የተደራጀ፤ በህብረተሰቡ ዘንድ ተዓማኒነትን ያተረፈ፤ የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ፤ የዳበረ የሲቪል ማህበረሰብ ተፈጥሮ ማየት እንደሆነ የገለጹት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገንዘብ ሚኒስቴር የቀረጥ ነፃ አጠቃቀምን አስመልክቶ ካወጣው መመሪያ ቁጥር 942/2015 ጋር በተያያዘ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የአፋፃፀም ችግር እየገጠማቸው ስለመሆኑ በተለያዩ የምክክርና የውይይት መድረኮች ላይ ሲነሳ በመቆየቱና በርካታ ሪፖርቶችና ቅሬታዎች ጭምር ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እየቀረበ በመሆኑ ይህንን ጉዳይ ማዕከል በማድረግ ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት በማድረግ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚቀመጥበትን መንገድ ማመቻቸት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የምክክር መድረኩ ሊዘጋጅ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ በበኩላቸው በሰብአዊ ድጋፍና በልማት ላይ የሚሳተፉ ድርጅቶች የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻልና በአደጋ የተጎዱ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም እንዲሁም ድንገተኛ አደጋ ሲከሰት የአስቸኳይ ግዜ ድጋፍ በማቅረብ ረገድ አይተኬ ሚና እንደሚጫወቱ እሙን ነው ፤ እነዚህ ድርጅቶች ለህብረተሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት ክፍያ የሚጠየቅበት ወይም ትርፍ የሚገኝበት ስራ አይደለም፤ አገልግሎቶቹ ሰብአዊ ከመሆናቸው አንጻር ቁልፍ የንግድ መርህ የሆነውን ትርፍ የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ እንደማይከተሉ አንስተዋል፡፡
ይህ አስራር በመላው ዓለም ስለሚታውቅ በርካታ ሀገሮች የሰብአዊ ድጋፍ ላይ ለሚሰሩ ድርጅቶች የቀረጥ ነጻ መብትን ጨምሮ በርካታ ማበረታቻዎችን ይሰጣሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በሀገራችንም በተወሰነ መልኩ ይህ ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውሰው ይህ ምክክር በቅርቡ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል በጸደቀው አዲስ መመርያ ቁጥር 942/2015 ላይ እና የመመርያውን አፈጻጸም ተከትሎ በተከሰቱ የአሰራር ችግሮች ላይ ሀሳብ ለመለዋወጥ የተዘጋጀ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በመድረኩ መነሻ የውይይት ሃሳብ እንዲሁም አቶ ጎሳ ተፈራ በገንዘብ ሚንስቴር ቀጥታ ያልሆኑ ታክሶች ቡድን መሪ ከታክስ ነጻ የአገልግሎት አሰጣጥን በሚመለከት መነሻ ጽሑፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በገንዘብ ሚንስቴር የታክስ ፖሊሲ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙላይ ወልዱ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችና ማብራሪያዎች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በተለይም መንግስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ ዋነኛ የልማት አጋር እንደሆኑ ጠቅሰው ዘርፉን ሊያግዙና ሊደግፉ የሚችሉ በርካታ ምቹ የአሰራር ሁኔታዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡