የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚተዳደሩበት ረቂቅ አዋጅ ለውይይት አቅርቧል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአዋጅ 1113/2011 በተሰጠው ስልጣን መሰረት ክልሎች የሚጠቀሙባቸው አዋጆች እንዲያወጡና እንዲያፀድቁ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ የአማራ ክልል የፍትሕ ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር አያሌው ቢሻው ከእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት የወጣው ረቂቅ ህጉ አሳሪ የሆኑ አሰራሮችን በማስተካከል ድርጅቶቹ ለማህበረሰቡ የላቀ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል። በውይይቱ ላይ የተገኙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደገለፁት አዋጁ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ያነሷቸው የነበሩ ቅሬታዎችን ሊፈታ የሚችልና ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በሀላፊነት እንዲያከናውኑ የሚያስችል ነው ብለዋል።
አያይዘውም ባለስልጣን መስሪቤቱ ከክልልና ከፌደራል ባለድርሻ አካላት ጋር በየአራት ወሩ በሚያደርገው ጉባኤ ላይ አምስት ክልሎች ባለስልጣኑ ከሚጠቀምባቸው አዋጆች ጋር ተመሳሳይ የሆኑ አዋጆችን አፅድቀው ወደ ስራ መግባታቸውን እንዳነሱ ገልጸዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለልማት፣ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እና ለሀገረ መንግስት ግንባታ አጋር ናቸው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ለድርጅቶቹ ምቹ ሁኔታን መፍጠርና ድጋፍ ማድረግም ከመንግስት ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል። በመጨረሻም የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ እና ፋይናንስ ቢሮ ረቂቅ አዋጁን በትኩረት ሰርተው በማዘጋጀታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡