ሶስተኛ ዙር የሚዲያ ሃላፊዎች የመስክ ምልከታ የሐረር ካቶሊክ ሰርቪስ እና የDRA ስራዎችን በመመልከት ተጠናቋል፡፡

ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች የተሳተፉበት የመስክ ጉብኝት በድሬዳዋ፣ ሀረር እና ጅግጅጋ ለተከታታይ አምስት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ በስኬት ተጠናቋል፡፡ በጉብኝቱ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ሀገር በቀልና የውጪ ድርጅቶች ስራዎቻቸውን ለሚዲያ አካላት ያስጎበኙ ሲሆን በተለይም በስደተኞችና ህጻናት ላይ፣ በኢኮኖሚ አቅም ግንባታ እና የስራ እድል ፈጠራ፣ ቁጠባ፣በውኃና በአካባቢ ጥበቃ፣ በትምህርትና መሰረተ ልማት እንዲሁም በጎዳና ህጻናት ጤናና ትምህርት ላይ የሚሰሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በጉብኝቱ ተዳሰዋል፡፡
የጉብኝቱ ማጠቃለያ በጅግጅጋ ከተማ ሲካሄድ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ምክትል ቢሮ ሀላፊ አቶ ሙሁዲን እንዲሁም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ ተገኝተዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደገለጹት በዚህ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የመስክ ምልከታ ከሌላው ጊዜ በተለየ የተለያዩ የመንግስት ኃላፊዎችን አሳትፈን ስኬታማ ጉብኝት አድርገናል ያሉ ሲሆን በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከሪፖርት ባለፈ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት እንዲመለከቱና ተገንዝበው ለማህበረሰቡ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ ጠይቀዋል፡፡ ከእኛ የተሻለ የዚህችን ሀገር ችግር ሊፈታ የሚችል የለም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በትብብር መስራት እንዲሁም ማህበረሰቡን ታች ድረስ ወርዶ ማገልገል ትልቅ ስኬት መሆኑን አንስተዋል፡፡ ለዚህም የታዩት ፕሮጀክቶች ትልቅ ማሳያ እንደሚሆኑ አንስተው ሚዲያውም ቀረብ ብሎ ለህዝብ ማስተዋወቅ ይጠበቅበታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዘርፉ በተሻለ ቁመና ላይ እንዲገኝ በርካታ ጥረቶችን እያደረገ እንደሚገኝ አንስተው ዘርፉ ለሀገር ልማትና እድገት ከዚህ በተሻለ ውጤታማ ስራ እንዲሰራ ሚዲያው ሊያግዝ ይገባል ብለዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ በበኩላቸው በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና በመንግስት መካከል ሰፊ መጠራጠሮች እንደነበሩ አንስተው አሁን ግን ከምንግዜውም በላይ ተቀራርበን እየሰራን ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት መካከል ጠንካራ ግንኙነት በመኖሩ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተው የሚዲያ ተቋማትም ከምክር ቤቱ እና ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በጋራ በመስራት የሲቪል ማህበረሰብ ዘርፉን የሚመለከቱ መርኃ ግብሮችን በመቅረጽ በሚኖራቸው ፕሮግራም ላይ ቢያካትቷቸው የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የፋይናንስ ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙሁዲን ባስተላለፉት መልዕክት የመገናኛ ብዙኃን ትክክለኛ መረጃ ለህብረተሰቡ ማድረስ እንደሚጠበቅባቸው አንስተው በተለይ ማህበረሰቡ በርካታ ስራዎች እንዲሰሩለት ይፈልጋል፤ ይህንንም ባለንበት ቦታ ሁሉ በኃቀኝነትና ህብረተሰቡን ሊጠቅም በሚችል መንገድ ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የመገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተመለከቱት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቃሴ መደሰታቸውን ገልጸው ከፕሮጀክት ዘላቂነት እና አሳታፊነት፣ ከአሰራር ስርዓት፣ ከፕሮጀክት አተገባበር፣ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ስላለ ግንኙነት፣ መረጃን ለህዝብ ከማድረስ፣ ስለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የክትትል ስርዓት ጋር በተያያዘ እንዲሁም ግንዛቤን ከመፍጠር ጋር የተያያዙ በርካታ ጥያቄዎችን አንስተው በሃላፊዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡