ሶስተኛ ዙር የሚዲያ ምልከታ በድሬደዋ፣ሐረር እና ጂግጂጋ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንና በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የጋራ አዘጋጅነት የሚዲያ አካላት የመስክ ምልከታ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ለሚዲያ ተቋማት ሃላፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት ማህበረሰቡ ውስጥ ስለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተለያዩ እሳቤዎች መኖራቸውን ገልጸው ጥሩውን ከመጥፎው የመለየትና ህብረተሰቡ ስለዚህ ዘርፍ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ሂደት ውስጥ ሚዲያ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡
አክለውም ከለውጡ በኋላ እንደ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሁሉ ለሚዲያ ዘርፉም መንግስት ልዩ ትኩረት በመስጠት የህግና የአሰራር ማሻሻያዎች ማድረጉን አንስተው ከዚህ የተነሳ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በሰብአዊ መብት አያያዝ፣ ሙስናንና ብልሹ አሰራሮችን ከመዋጋት አኳያ ሚዲያና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን አስተዋኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ ከዚህ የበለጠም እንዲያበረክቱ ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የሀሳብ ብዝሃነት እንዲዳብር፤ ፖለቲካዊና አገራዊ ችግሮች በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱ፤ በውይይትና በምክንያታዊነት የሚያምን ትውልድ እንዲፈጠር በተለይ ሚዲያ አይተኬ ሚና እንዳለው በመግለጽ ማህበረሰባችን በመረጃ እጦት ወይም በተዛባ መረጃ ምክንያት ለችግር እንዳይጋለጥ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንድትወጡ በዚሁ አጋጣሚ አደራ ለማለት እወዳለሁ ሲሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የመስክ ምልከታው በድሬደዋ አስተዳደር የሚንቀሳቀሱትን አዎንታዊ ምላሽ ለልማት (PAD) እና ቸሻየር ኢትዮጵያ የተባሉ ሁለት ሀገር በቀል ድርጅቶችን እንዲሁም በሶማሌ ብሄራዊ ክልል ሽንሌ ወረዳ ኢንተርናሽናል ሬስኪዩ ኮሚቴ (IRC) የተባለ የውጪ ድርጅት እያደረገ የሚገኘውን የስራ እንቅስቃሴ በመመለልከት ተጀምሯል፡፡ ከመስክ ምልከታው አስቀድሞ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባለፉት 4 አመታት የተሰሩ የለውጥ ስራዎችን እንዲሁም በዘርፉ የታዩ መሻሻሎችን በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክርቤት ዋና ዳየሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ በበኩላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤትን በሚመለከት ለተሳታፊዎች ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ለተነሱላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች በጋራ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ምልከታ የተደረገባቸው ድርጅቶች በስደተኞች፣በእናቶች፣ ህጻናት ፣ውሃ፣ በስራ እድልና አቅም ግንባታ እንዲሁም በአካል ጉዳተኞች ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ናቸው፡፡ ቡድኑ በቀጣይ ሶስት ቀናት በሀረሪ ብሄራዊ ክልል እንዲሁም በሶማሌ ብሄራዊ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የስራ እንቅስቃሴ የሚመለከቱ ይሆናል፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ የተዘጋጀው የሚዲያ ምልከታ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ስራ በማስተዋወቅ የዘርፉን ሚና ለማጎልበትና የሁለቱን ተቋማት ተግባርና ሃላፊነት ለሚዲያ አካላት ማስተዋወቅ ነው፡