የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ልዩ ልዩ የስራ ክፍሎች የተውጣጡ ሰራተኞችና ባለሙያዎች የጌርጌሴኖን የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማህበርን ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝቱ ላይ የተቋሙ ሰራተኞች በበጎ ፈቃድ ወደ ማህበሩ ቀርበው የሚቻላቸውን ሁሉ ለማድረግም ቃል ገብተዋል፡፡ በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በማዕከሉ ያዩት ነገር ከጠበቁት በላይ መሆኑን አንስተው በማህበሩ እየተሰራ ያለው ስራ መልካም ልብ ያለው፣ ለሀገር የሚቆረቆሩ እና ማህበረሰባቸውን የሚወዱ፣ ደግና ቅን የሆኑ የሚሰሩት መልካም ስራ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ጥቂት ድጋፍ ቢደረግላቸው ሀገራቸውን እና ማህበረሰባቸውን ሊቀይሩ የሚችሉ በርካታ ዜጎች በየቦታው ወድቀው የሚገኙ መሆናቸውን ያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጌርጌሴኖን ከወደቁበት አንስቶ ባደረገው ድጋፍ ጤናቸው ተመልሶ በስራ ላይ መገኘታቸውን ማየት ችለናል ብለዋል፡፡ ድርጅቱ ውጤታማ እንዲሆን በጎ ፈቃደኞችን ማሳተፍ፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅትና በትብብር መስራት እንዲሁም ራስን ማስተዋወቅ የበለጠ ውጤት ለማምጣት በእጅጉ እንደሚረዳ ያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አቅም በፈቀደ መጠን ሁሉ የሚችለውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ የጌርጌሴኖን የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማህበርን ጎበኙ፡፡

በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የበጎ ፈቃድ ማጎልበትና ትብብር መሪ ስራ አስፈጻሚ አስተባባሪነት የተሰባሰቡ የተለያዩ አልባሳትን ለማህበሩ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሰራተኞችም በበጎ ፈቃድ ማህበሩን ለማገዝ ቃል ገብተዋል፡: የጌርጌሴኖን የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማህበር መስራችና ስራ አስኪያጅ ሊቀ ህሩያን መለሰ አየለ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ኃላፊዎችና ሰራተኞች መጥተው ስለጎበኟቸው ምስጋናቸውን አቅርበው ወደፊት ባላቸው ጥቂት ቦታና የሰው ኃይል በርካታ ስራዎችን ለመስራት እቅድ መያዛቸውን ገልጸዋል፡፡ ጌርጌሴኖን የአእምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ከ18 ዓመት በፊት የተቋቋመ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሲሆን በጎዳና ላይ የወደቁ የአእምሮ ህሙማንን በማንሳት ወደቀደመ ጤንነታቸው እንዲመለሱ እያደረገ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡ በማዕከሉ 567 የአእምሮ ህሙማን የሚገኙ ሲሆን ከ20 በላይ የሚሆኑት ድነው በድርጅቱ ውስጥ በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡