የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከ voluntary service overseas (VSO) ጋር በመተባበር የበጎ ፈቃደኝነት ባህልን በማህበረሰቡ ውስጥ ለማሳደግ የመንግስት አካላት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስለሚኖራቸው ሚና እንዲሁም በሀገር አቀፍ ፕሮግራሞች ያሉ የበጎ ፈቃደኝነት ተመክሮዎች ላይ ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የበጎ ፈቃደኝነትና በጎ አድራጊነት ባህልን በማህበረሰቡ ውስጥ የማሳደግ ኃላፊነት በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ተሰጥቶታል፡፡ ይህንኑ ኃላፊነት ለመወጣት በርካታ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በዛሬው ዕለት ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት እና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ጋር በጎ ፈቃደኝነትን በማህበረሰቡ ውስጥ ባህል ለማድረግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም የመንግስት ባለድርሻ አካላት ስለሚኖራቸው ሚና እንዲሁም በሀገር አቀፍ ፕሮግራሞች ያሉ ምርጥ ተመክሮዎችን በሚመለከት ውይይት አድርጓል፡፡
በዚሁ የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ የበጎ ፈቃድ ጽንሰ ኃሳብ ከሰብዓዊ አመለካከት በመነሳት ለማህበረሰብ እድገት፣ ልማት፣ ብልጽግና በራስ ተነሳሽነት፣ እውቀት፣ ገንዘብ እና መሰል ነገሮች መስራት፤ በምላሹ ደግሞ እውቀት፣ ልምድና ክህሎትን ማዳበር እንደሆነ አንስተው በሀገራችን ዜጎች ማህበራዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት በተለያየ መንገድ የበጎ ፈቃድ ጽንሰ ሀሳብን ሲተገብሩት እንደቆዩ አንስተዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ይህን የበጎ ፈቃደኝነትና በጎ አድራጊነት ባህልን ለማሳደግ በአስር አመት ስትራተጂክ እቅድ ውስጥ ቅድሚያ ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ የበጎ ፈቃደኝነት ባህልን ማሳደግ እንዱ እንደሆነ አንስተው ይህንኑ ቅድሚያ ሰጥቶ ለመምራት የበጎ ፈቃድ ማጎልበትና ትብብር መሪ ስራ አስፈጻሚ በሚል የስራ ክፍል አቋቁሞ በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
የመድረኩ ዓላማ የበጎ ፈቃደኝነት ባህልን በማህበረሰቡ ውስጥ ባህል ለማድረግ የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሚና ምን መሆን እንደሚገባው ማመላከት ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ከውጪ ድጋፍ በመላቀቅ በውስጥ አቅም ችግሮቻችንን ለመቅረፍ እንዲሁም ቀደም ሲል እንደሰራናቸው ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለመስራት መንግስት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የግሉ ዘርፍ በቅንጅት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ አያይዘውም በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ የሆነ የበጎ ፈቃደኝነት ፖሊሲ አለመኖር እንዲሁም እሱን የሚያስተባብርና የሚመራ የመንግስት ተቋም አለመኖሩ በዋናነት እንደ ችግር የሚነሳ መሆኑን አንስተው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይህንን ለመቅረፍ ጥረቶችን እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
የበጎ ፈቃኝነት ስራን እዚህም እዚያም በተበጣጠሰ ሁኔታ እየተሰራ ይገኛል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የበጎ ፈቃድ ፖሊሲው ከወጣ በኋላ ተቋማዊ ቅርጽ ይዞ ተግባራዊ እንደሚሆንም አንስተዋል፡፡
Voluntary service overseas (VSO) ግሎባል ዩዝ ኢንጌጅመንት ማኔጀር ወ/ሮ ሶስና ይርጋ በበኩላቸው የበጎ ፈቃደኝነት ጽንሰ ሀሳብን በማህበረሰቡ ውስጥ የማስረጽ ኃላፊነት የአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ አለመሆኑን አንስተው voluntary service overseas VSO በዋናነት የበጎ ፈቃደኝነትን ጽንሰ ሀሳብን ማስተዋወቅ እና እድገትና ልማትን በመደገፍ ለውጥ ማምጣትን አላማ አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡