የስርዓተ ጾታ እና ማህበራዊ አካታችነት ስትራቴጂ የትውውቅና የስልጠና መርኃ ግብር ተካሄደ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከCSSP2 ጋር በመተባበር ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ከፍተኛ ባለሙያዎች በስርዓተ ጾታ እና ማህበራዊ አካታችነት ስትራቴጂ እቅድ ዙሪያ የትውውቅ እና የስልጠና መርኃ ግብር አካሂዷል፡፡ በስልጠናው ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦን ጨምሮ የተቋሙ የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ስልጠናው ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችንና ልዩ ድጋፍ የሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች በእለት ከእለት የስራ እንቅስቃሴ ውስጥ አካቶ መተግበር ስለሚቻልባቸው መንገዶች ሰፊ ገለጻ ተደርጓል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በንግግራቸው የሚሰጡ ስልጠናዎችን በትክክል መጠቀም ከቻልን ብዙ ነገር መለወጥ የምንችል በመሆኑ የሚገኙ የስልጠና ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ሞዴል ተቋም እንዲሆን የምንፈልግ በመሆኑ ዕውቀትን ከስነምግባር ጋር የያዘ ባለሙያ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ እንዲህ አይነት ስልጠናዎች እንደሚዘጋጁ ገልጸዋል፡፡
ሴቶች በማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዬች ላይ ያላቸው ተሳትፎ በቂ ባለመሆኑ ዛሬም የሴቶች ጉዳይ አጀንዳ ሆኖ እንወያያለን ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ሴቶች እኩል ተጠቃሚ መሆን እስኪችሉ ሁላችንም ጥረት ማድረግ ይገባናል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ይህንን ሰነድ የባለሰስልጣን መስሪያ ቤቱ የስራ መሪዎች አውቀውት በቀጣይ ወደሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የማውረድ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡ መርኃግብሩን ላዘጋጀው CSSP2ም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡