የአባቶቻችንን አደራ በመወጣት አንድነቷንና የዜጎቿን ክብር የተጠበቀ ጠንካራ አገር ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር ገለጹ፡፡

ለ127ኛ ጊዜ የሚከበረው የአደዋ ድል በዓል “ዓደዋ አንድነት፣ ጀግንነትና ጽናት” በሚል መሪ ቃል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከጥንታዊ አርበኞች ማህበር እና ከኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች ማህበር እንዲሁም ከተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር አከበረ፡፡ በበዓሉ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስርያ ቤቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደተናገሩት ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪክ ሂደት ውስጥ በተለያዩ ዘመናት በርካታ የህልውና ተግዳሮቶች ተደቅነውባት በኢትዮጵያዊያን በተከፈለ መስዋትነት በድል አድራጊነት ተግዳሮቶችን በሙሉ በመሻገር የፀናች ታላቅ አገር መሆኗን ገልፀዋል፡፡ አገራችን በተለያዩ መስኮች የሚያጋጥሟትን ፈታኝ ሁኔታዎች ከሁላችን ለሁላችን በሆነው በደማቁ የጋራችን የአድዋ ድል ትሩፋቶች ውስጥ ሁነን ለሁላችንም ምቹ የሆነች ፣ የለማች ዴሞክራሲያዊትና ሰላሟ የተጠበቀ አገር የመገንባትና ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ በአደዋ ጦርነት መስዋትነት የከፈሉ አባቶቻችን አደራ አለብን ሲሉ ም/ዋና ዳይሬክተሩ አንስተዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የአደዋ ድል በኢትዮጵያ በአፍሪካ እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ በተገቢው መንገድ እንዲከበር የማድረግ እና የአድዋ ትሩፋቶችን በመጠቀም ትውልድ የመገንባት ሃላፊነት እንዳለባቸው በመግለጽ ፈታኝ አገራዊ ችግሮቻችን በዘላቂነት ተፈተው የለማች ዴሞክራሲያዊት እና ሰላሟ የተጠበቀ አገር በመገንባት ሂደት ላይ በንቃት እንዲንቀሳቀሱ በባለስልጣን መስረሪያ ቤቱ ስም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ከደማቁ የአድዋ ድል አገራዊ አንድነትን፣ልዩነታችን ጥንካሬያችን መሆኑን፣አብሮነትን፣ሀገር ወዳድነትን፤ከራስ ጥቅም በፊት የአገርን ጥቅም ማስቀደምን፣ጀግንነትን፣ጽናትን፣የአስተሳሰብ ልዕልናን፣በድል አለመታበይን፣የአመራር ጥበብን እንዲሁም ለጋራ ስኬት በጋራ መሰለፍን ልንማር እና በአሁኑ ወቅት በግል ህይወታችንና በተቋም እንቅስቃሴያችን ልንተገብረው የሚገባ መሆኑን ማስመር ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የአደዋ ድል የማይጠፋ አርማችን፣ የማያረጅ ጌጣችን፣ ከሩቅ የሚታይ ምልክታችን ፣ ዓለም የሰማው ድምጻችን፣ የተባበረ ክንዳችን እና ከፍ ያለ ክብራችን ነው ሲሉ በማንሳት በዓለም አደባባይ በኩራትና በአሸናፊነት ስሜት እንድንቆም መስዋት የሆኑ አባቶቻችንና እናቶቻችን ዘላለማዊ ክብር ይገባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ኮነሬል እስጢፋኖስ ገ/መስቀል የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ማህበር ፕሬዝዳንት የአድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ አጠቃላይ ያለፉበትን የድል ታሪክ ለታዳሚው አጋርተዋል፡፡ አቶ ተስፋዬ ሽፈራው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈጻሚ ለዕለቱ የተዘጋጀውን ሰነድ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡