ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በጅማ ዞን ለሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶችና በዞኑ ለሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጀቶች በመመሪያዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአዋጅ 1113/2011 በተሰጠው ስልጣን መሰረት መመሪያዎችን አዘጋጅቶ ለሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በዞን ደረጃ ስልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል ፡፡
በጅማ ዞን ለሚገኙ የመንግስት ተቋማትና ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በወጡ ስምንት መመሪያዎች ላይ በጅማ ከተማ እየተሰጠ ይገኛል፡፡
በስልጠናው ላይ የተገኙት የጅማ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሚፍታ አብድልቃድር እንዳሉት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያወጣቸውን መመሪያዎች ወደ ዞኖች አውርዶ መስጠቱ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አንስተው ዞኑ የስልጠናው እድል ተጠቃሚ በመሆኑ አመስግነዋል፡፡
ሀላፊው አያይዘውም በጅማ ዞን የሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከክልሉ መንግስት እና ከዞኑ ጋር የልማት ስራዎች በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን በመግለጽ በአሁን ወቅት በአገራችን እየተሰሩ ያሉት የልማት ስራዎች በመንግስት ብቻ የሚሸፈኑ ባለመሆናቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በልማት ስራዎች ላይ የሚታዩ ክፍተቶች በመሙላት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በጅማ ዞን እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች 14 የውጭ ድርጅቶች እና 18 አገር በቀል ድርጅቶች ሲሆኑ 53 ፕሮጀክቶች ተቀርፀው እየተተገበሩ ይገኛሉ፡፡
ስልጠናው በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ክትትል፣ግምገማና ምርመራ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተሾመ ወርቁ እና የፕሮጀክት አስተዳደርና ሀብት ማፈላለግ ዴስክ ሀላፊ አቶ እድሪስ የሱፍ እየተሰጠ ይገኛል፡፡