በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ የወጡ ህጎች እና መመሪያዎችን በአግባቡ ተረድቶ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅና አዋጁን መሰረት አድርጎ የተዘጋጁ መመሪያዎች ላይ ለማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሚመለከታቸው የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ድርጅቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተዘጋጀ፡፡ የባለስልጣን መስሪያቤቱ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ሲያደርጉ እንደገለጹት በባለፉት የሪፎርም ግዚያት ለውጥ ከተደረገባቸው ተቋማት መካከል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መሆኑን አንስተው በተለይም ዘርፉ ይተዳደርበት የነበረው አዋጅ 621/2001 ተሽሮ 1113/2011 ተግባራዊ አንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡
ህጉ ሲሻሻል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለልማት፣ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እና ለሃገረመንግስት ግንባታው የበኩላቸውን ሚና ይጫወታሉ በሚል መሆኑን የገለጹት ሃላፊው ህግን መሰረት ያደረገ እና የህዝብን ሞራል ተቃራኒ ባልሆኑ ጉዳዬች ሁሉ በመሰማራት የማህበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት እደሚቻል አንስተዋል፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ በባለፉት አራት ዓመታት ከተገልጋይ እርካታ አንጻር፣አገልግሎት አሰጣጡ ዘመናዊ ከማድረግ አንጻር፣ከክልሎች ጋር ያለው ቅንጅታዊ የአሰራር ስርዓትን ከማጎልበት አንጻር በርካታ ስራዎች መከናወኑን አብራርተዋል፡፡
ዘርፉ የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖረው ባለድርሻ አካላት ህጎችን በአግባቡ መረዳትና ተግባራዊ ማድረግ፣የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ያላቸውን እውቀትና ክህሎት በአግባቡ መጠቀም እና ቅንጅታዊ የአሰራር ስርዓትን በማጎልበት የማህበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በዛሬው ዕለትም የሪፎርሙ አካል የሆኑ ዝርዝር የተዘጋጁ መመሪያዎች ላይ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው አስፈጻሚ አካላት ህጉን በአግባቡ በመረዳታቸው እና መመሪያው በዝርዝር መዘጋጀቱ የዳበረ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ ለመፍጠር፣ በህግ ለመመራት እና ተፈጻሚ ለማድረግ ብሎም የሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች በዕለት ተዕለት ስራቸው የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመፍታት ያስችላል ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ሰላማዊት ነጋ የማዕከላዊ ጎንደር የገንዘብ መምሪያ ም/ሃላፊ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በማድረግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ህጎችን በአግባቡ አውቀን ተግባራዊ ማድረግ እንዲያስችለን እንዲህ አይነት ስልጠና ማዘጋጀቱን አመስግነዋል፡፡