በቅርቡ በፍትህ ሚኒስቴር ቁጥር ተሰጥቷቸው ስራ ላይ የዋሉትን መመሪያዎች በሚመለከት በሶማሌ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጅግጅጋ ከተማ እንዲሁም በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባህዳር ከተማ ለሚመለከታቸው የመንግስት ባለድርሻ አካላትና በክልሎቹ ለሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡

በጅግጅጋው መድረክ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደተናገሩት በአዋጅ 1113/2011 አንቀጽ 89 መሰረት አዋጁን ሊያስፈጽሙ የሚችሉ መመሪያዎች ባለስልጣን መስሪያቤቱ ማውጣት እንደሚችል በተደነገገው መሰረት ተቋሙ እስካሁ 17 መመርያዎችን በማዘጋጀት እና ከዚህ ውስጥ 8ቱ በባለስልጣኑ ቦርድ ቀርበው ማጸደቅ መቻሉን ተናግረዋል ፡፡ የነዚህም መመርያዎች አስፈላጊነት በህጎች ተዋረድ (Hierarchy of laws) መመርያ የመጨረሻ ወይም የበታች ህግ በመሆኑ በየደረጃው ላሉ አስፈፃሚ አካላት ጠቃሚነቱ የጎላ መሆኑ፣ በአዋጁ ያልተብራሩ ዝርዝር ጉዳዮች የሚብራሩበት እና አዋጁን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳትና ለማስፈፀም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አዋጅ ቁጥር 1113/2011 መውጣቱና የአሰራር ማሻሻያዎች መደረጋቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንቅስቀሴ ምህዳርን እንዲሰፋና በሀገር እድገት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲጨምር ማድረጉን ዋና ዳይሬክተሩ አክለው ተናግረዋል፡፡

በባህርዳር ከተማ በተደረገው ስልጠና ላይ የተገኙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደገለጹት በመጀመሪያው የለውጥ ምዕራፍ ውጤታማ የህግ እና ተቋማዊ ሪፎርም ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው በአራት ዓመታት ያሳካናቸውን ተግባራት ወደ ኋላ እንዳይመለሱ የማላቅ ስራዎች የሚሰራበት፣ስፔሻላይዜሽን ስራ ማጎልበት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራ መስራት የሁለተኛው የለውጥ ምዕራፍ ተግባራት እንደሚሆኑ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በፊት ከክልሎች ጋር ያለው ግንኙነት ደካማ እንደነበር ያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አሁን ግን ከክልሎች ባለፈ እስከታችኛው የዞን አደረጃጀት ድረስ ጥሩ ግንኙነት መፍጠር መቻሉን ጠቁመው ይህ የሪፎርም ስራ እንዲሳካ ሁላችንም በመተባበርና በጋራ መስራት ይጠይቀናል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ስልጠናዎቹ ትኩረት ያደረጉት ስለ ድርጅቶች መዋሃድ፣ መከፋፈል፣ መለወጥና መፍረስ የወጣ መመሪያ ቁጥር 936/2015፤ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ የሚሰማሩበትን ሁኔታ ለመወሰን የወጣ መመሪያ (937/2015)፤ የአገር በቀል ድርጅቶች ምዝገባ እና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 938/2015 እንዲሁም የጥቅም ግጭትን ለማስቀረት የወጣ መመሪያ ቁጥር 939/2015 በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሲሆን በቀጣይ ስልጠናው ባልተዳረሰባቸው የአፋር፣ ኦሮሚያ፣ ጋንቤላ፣ ሲዳማና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች የሚሰጥ ይሆናል፡፡
Click the button