ይህ የተባለው ለተቋሙ ወጣት ሴት ሰራተኞች የስብዕና ግንባታ እና የስሜት ብቃት በስራ ቦታ በሚል ርዕስ ስልጠና በተሰጠበት ወቅት ነው፡፡ ስልጠናው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከኒው ብራይት ኮሚኒውቲ ዴቨሎፕመንት ሴንተር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው፡፡ በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደገለጹት በሃገራችን አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ወጣት መሆኑን አንስተው ወጣትነት የነገ ሃገር ተረካቢ እና የዛሬ የሃገር ባለቤት ናቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ወጣትነት በዋዛ ፈዛዛ የምናባክነው ሳይሆን ዛሬ የጣልነው መሰረት ለነገ ተስፋና መሰረት የምንጥልበት መሆኑን አንስተው ወጣትነት ካለፈ የማይመለስ እና ሳንሰራ ካለፍንበት የሚቆጭ በመሆኑ ቁጭት ውስጥ የሚከት ነገር ውስጥ ማለፍ የለብንም ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ወጣት ብዙ ፈተናዎች አለበት ሴት ወጣት ሲኮን ደግሞ የበለጠ ችግሩ ይጨምራል ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሩ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ወደ እድል የምትቀይሩ እና የጥንካሬ ምንጭ አድርጋችሁ እንደምትሰሩ አምናለሁ ብለዋል፡፡
ወጣቶች እንደተቋማችን ብዙ ሃላፊነት አለባችሁ በማለት ወጣት ሴቶችና ወንዶችን አብቅቶ በአግባቡ መምራት ከተቻለ የበለጸገች ሃገር መፍጠር ያስችላል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ለወጣቶች እደዚህ አይነት ስልጠናዎች ሲዘጋጁ አቅም የምትገነቡበት እና ልምድ የምትቀምሩበት ሲሆን ዛሬ አቅማችሁን በመገንባት ለተቋማችሁ ብሎም ለሃገር የተሻለ ስራ ትሰራላችሁ ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ሁልግዜ የማያቋርጥ ለውጥ ውስጥ ማለፍ ያስፈልጋል ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሩ ስልጠና ስንወስድ ከስልጠና በኋላ ምን አዲስ ነገር አገኘን ብሎ መጠየቅና በስልጠናው እራሳችንን መለወጥ ብሎም በስልጠናው መጠቀም ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በመጨረሻም ለኒው ብራይት ኮሚኒውቲ ዴቨሎፕመንት ሴንተር ስልጠናውን በማስተባበርና ወጪውን በመሸፈን ላበረከተው አስተዋጽኦ የምስጋና የምስክር ወረቀት በተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ተበርክቶላቸዋል፡