በሪፖርቱ ተቋሙ ካስቀመጣቸው ግቦች አንጻር የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ የተገኙ ውጤቶች፣ያጋጠሙ ችግሮች የተወሰዱ እርምጃዎች፣ እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫን ያካተተ ሪፖርት በወ/ሮ ቃልኪዳን መንግስቴ የስትራቴጂክ ጉዳዬች ስራ አስፈጻሚ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በውይይቱ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደገለጹት በባለፉት ዓመታትም ሆነ ወራት የተከናወኑ ስራዎች በጣም አበረታች መሆናቸውን አንስተው በመተባበርና በመተጋገዝ ከዚህ የተሻለ ስራ ለመስራት መዘጋጀት አለብን ብለዋል፡፡ የተቋሙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው የባለፉት 4 ዓመታት የመጀመሪያው የሪፎርም ምዕራፍ መሆኑን አንስተው በዚህ ሂደት የህግ ሪፎርም ማሳካት መቻሉ፣ የአቅም ግንባታ ስራዎች ፣የአሰራር ስርዓት መዘርጋት፣ጠንካራ ቅንጅታዊ የአሰራር ስርዓት ማጎልበት እና ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ መቻሉ በዘርፉ የመጡ ስኬቶች መሆናውን አንስተዋል፡፡ አያይዘውም ይህንን በማሳካታችን የአገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል መታየቱ፣በክህሎት የተገነባ ተቋም መፈጠሩ፣ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በአጋነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መፈጠር መቻሉና በዘርፉ እና ስለተቋሙ በጎ የሆነ ገጽታ መገንባቱ የመጡ ለውጦች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ ሁለተኛው ተቋማዊ ሪፎርም በአራት ዓመታት ያሳካናቸውን ተግባራት ወደ ኋላ እንዳይመለሱ የማላቅ ስራዎች የሚሰራበት፣ስፔሻላይዜሽን ስራ ማጎልበት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራ መስራት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አክለው አንስተዋል፡፡