የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከCSSP-2 ጋር በመተባበር ለአገልግሎት ሰጪ ባለሙያዎቹ በተቋሙ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ለመግባት በሂደት ላይ በሚገኘው ከጥቃት ጥበቃ መምሪያ /Safeguarding Guideline/ እና በቡድን ግንባታ (Team Building) ዙሪያ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በስልጠና መድረኩ ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ባለስልጣን መ/ቤቱ ላለፉት የሪፎርም ዓመታት በበርካታ የለውጥ ሂደት ውስጥ ያለፈ መሆኑን በማውሳት በሂደቱም አበረታች ስኬቶች ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀው በአሁኑ ወቅት አዲስ መዋቅራዊ አደረጃጀት በማዘጋጀት ሰራተኞችን ደልድሎ ወደ ሁለተኛ የተቋማዊ የሪፎርም ምእራፍ ውስጥ እየገባ ስለሆነ መላው የተቋሙ ባልደረቦች አሁን ያለንበትን ሁኔታና ተቋማዊ የትኩረት መስኮችን ለማሳካት የሚያስፈልገውን እውቀት፣ ክህሎትና ስነ-ምግባር በመያዝ ዝግጁ መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ አያይዘውም አሁን የምንገኝበት የሪፎርም ምእራፍ ያለፉትን የለውጥ ስኬቶች የበለጠ የምናፀናበት፣ በአፈፃፀማችን ስፔሻላይዝ የምናደርገበት እንዲሁም ዲጂታል ተቋም የምንገነባበት ይሆናል ብለዋል፡፡

ስለሆም በተቋሙ በተከታታይ እየተሰጡ ያሉ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን ብቁ፣ ውጤታማና መንግስትና ህዝብ የሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ በመወጣት መልካም ስም ያተረፈ ተቋም የመገንባት አካል መሆኑን በመገንዘብ ስልጠናዎችን ራስን በማሻሻል፣ ሃላፊነትን ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መንገድ በመወጣት በተግባር መተርጎም ከእያንዳንዱ አመራርና ባለሙያ የሚጠበቅ መሆኑን አስመረውበታል፡፡ በSafeguarding Guideline ዙሪያ የሚሰጠው ስልጠናም በማናቸውም መንገድ የሚፈፀም ጥቃትና ትንኮሳን የሚጠየፍና ለእነዚህ ተግባራት ቦታ የሌለው ለሰራተኞቹም ሆነ ለተገልጋዮች ምቹ የሆነ ተቋም የመገንባት አካል ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡