የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከsave the children እና ከMSF Holland የተገኙ ተሽከርካሪዎችን ለተለያዩ ሀገር በቀል ድርጅቶች አስተላልፏል፡፡ ተሽከርካሪዎቹ የተላለፉት ለፈለገ አረጋዊያን መርጃ ማህበር፣ ለሰሊሆም የአእምሮ ህሙማን መርጃ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን መርጃ ማህበር፣ ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን መርጃ ድርጅት፣ አቡነ ዜና ማርቆስ የህጻናትና አረጋውያን መርጃ ድርጅት፣ አክሽን ፎር ዘ ኒዲ እና ፌዝ ኢን አክሽን ለተባሉ ሰባት ሀገር በቀል ድርጅቶች ነው፡፡ ተሸከርካሪዎቹን ቦታው ድረስ በመሄድ ያስተላለፉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ሀገር በቀል ድርጅቶች የማህበረሰቡን ስነ ልቦናና ባህል የሚያውቁና ተደራሽነታቸውም ላቅ ያለ በመሆኑ ከውጪ ድርጅቶች ጋር በቅንጅትና በትብብር መስራት ይኖርባቸዋል ያሉ ሲሆን በርካታ የውጪ ድርጅቶች ሀገር በቀል ድርጅቶችን እየደገፉ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት ጊዚያት በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ማለፏን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ እንደ MSF Holland ያሉ ድርጅቶች ያለእረፍት ሁኔታዎች እንዲስተካከሉ ማድረግ መቻላቸውንና አሁን ላይ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በርካታ ስራዎችን በጋራ መስራት በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከSave the children አምስት እንዲሁም ከMSF Holland ሁለት መኪኖች የተላለፉ ሲሆን የሁሉም ድርጅቶች የስራ ኃላፊዎችና ተወካዮች በተገኙበት ተረክበዋል፡፡ ሀገር በቀል ድርጅቶቹም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱና ሴቭ ዘ ቺልድረን እንዲሁም MSF Holland ላደረጉላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡