በኢፌዲሪ ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በሜሬጆይ ኢትዮጵያ አስተባባሪነት በዜጎች የጎዳና ተጋላጭነት ላይ የተቀናጀ ምላሽ ለመስጠት የፖሊሲ አውጪዎች፣አስፈፃሚና የባለድርሻ አካላት መድረክ ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል ተካሄዷል ፡፡ በመድረኩ መልዕክት ያስተላለፉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንዳሉት በሀገራችን ኢትዮጵያ የዜጎችን ደህንነትና የመኖር ዋስትና ከማስጠበቅ አኳያ ከመንግስት ጎን ለጎን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አይተኬ ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባ በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 ሃላፊነት የተጣለባቸው ሲሆን በዋነኝነት በማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲው ማዕቀፍ ላይ የተጠቀሱትን የህብረተሰቡን የስራ እድልና የኑሮ ሁኔታን ማሻሻል፣ የማህበራዊ መድን አገልግሎትንና ልማታዊ ሴፍቲኔትን ማስፋፋት፣የመሰረታዊ አገልግሎትንና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማሳደግና ለጥቃትና ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች የህግ ጥበቃና ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አመላክተዋል ፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚያከናውናቸው ሥራዎች ዘላቂ ልማትን የሚያመጡና ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት የሚያስችሉ በተለይም ለጠቅላላው ሕዝብ ወይም ለሦስተኛ ወገን ጥቅም መሥራትን ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ድርጅት፣ የሴቶችን፣ ህጻናትን፣ የአካል ጉዳተኞችን፣ የአረጋውያንንና ሌሎች ለጉዳት ተጋላጭ ወይም ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጥቅምን ማካተቱን ማረጋገጥ አለበት ብለዋል ፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የዜጎችን ጎዳና ተጋላጭ ለመቀነስ እና የማህበረሰቡን ማህበራዊ ደህንነት ዋስትና በሚያረጋግጡ ተግባራት ላይ በመሳተፍ በህግ የተጣለባቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ አደራ በማለት እንደባለስልጣን መስሪያቤታችን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ያለንን አጋርነት በማጠናከር የማህበረሰቡን ማህበራዊ ደህንነት ዋስትና ለማረጋገጥ ያለኝን ቁርጠኝነት እገልጻለሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በመድረኩም የኤ.ፌ.ድሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ክብርት ዶክተር ኤርጎግን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ሃላፊዎችና የግል ባለሃብት እንዲሁም የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶች ተሳታ ሆነዋል ፡፡