አዲስ አበባ (ኢዜአ) ታህሳስ 19/2015 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለዘላቂ ሰላምና አብሮነት ትኩረት በመስጠት በአገር ግንባታ ሂደት ላይ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተጠየቀ። ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች “በሀገር ግንባታ የምሁራን ሚና” በሚል ርዕሰ ጉዳይ በአዲስ አበባ ውይይት አካሂደዋል። በውይይቱም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፣ የሴቶችና የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዲሁም የሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አመራሮችና ተወካዮች ተገኝተዋል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጂማ ዲልቦ፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የሲቪል ሚህበረሰብ ድርጅቶች በሀገሪቱ ልማት ሰላምና ዴሞክራሲ ላይ ያላቸውን ሚና ለማጠናከር መንግስት የአሰራርና የህግጋት ማሻሻያ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
ይህን ተከትሎም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድህነትን እና ኋላቀርነትን ለማስወገድ በማህበረሰብ ማንቃት በድጋፍና በምርምር መስክ እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል። የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ ባቀረቡት የመወያያ ፅሑፍ መንግስት ምቹ የፖለቲካ ምህዳር ለመፍጠር ካከናወናቸው የለውጥ ስራዎች መካከል የሲቪል ማህበራት አዋጅ ማሻሻያም ተጠቃሽ ነው ብለዋል። ይህን ተከትሎም ሀገር በቀል ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች በሀገራቸው የሰላምና የልማት ሂደት በጎ ሚና እንዲጫወቱ በር ከፍቷል ነው ያሉት። ከዚህ አኳያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሀገርን ጥቅም በማስጠበቅና በሰላምና ዴሞክራሲ መጠናከር ላይ አተኩረው መሥራት እንዳለባቸው በመጠቆም። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ፤ ጠንካራ ሀገር እውን ለማድረግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሀሳብ ብዝሃነት እንዲዳብርና ዴሞክራሲ እንዲጎለብት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ማከናወን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል መንግስት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አንስተው፤ የሀገር ግንባታው እውን እንዲሆን ሁሉም ዜጋና ተቋማት ለሰላም ቀናኢ ሆነው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ በአፅነኦት ተናግረዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ በሚፈለገው ልክ ለማስቀጠል ብቁ ተቋማትን ለመፍጠር ራሳቸው አርዓያ ሆነው እንዲሰሩም ጠይቀዋል። የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ህልውናውን አስጠብቃ እንድትቀጥል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በጎ ሚና መጫወታቸውን አንስተዋል። ሆኖም ሀገርን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት በማላቀቅ ረገድ ግን የሚጠበቅበቸውን እንዳልተወጡ አንስተው፤ የሀገር ግንባታ ሂደቱ ላይ በጎ ሚናቸውን ለመወጣት በቅንጅትና በአንድነት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። በውይይቱ የተሳተፉ የሲቪል ማሀብረሰብ ድርጅት ተወካዮች በበኩላቸው ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምቹ የህግና የአሰራር ምህዳር መፈጠሩን አድንቀዋል። በመሆኑም የአገርና ህዝብ ጥቅምን በማስጠበቅ ጠንካራ አገር ለመገንባት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡