የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር በተለያዩ ጊዚያት ድጋፍ ማድረጉ ተገልጷል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ የክልሉን ፕረዝዳንት አቶ አወል አርባ ጨምሮ ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ጋር በዚሁ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ በንግግራቸው እንደገለጹት በሃገራችን በተከሰተው ጦርነት የደረሰውን አደጋ ለመቅረፍ እንዲሁም ለተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ድጋፍ ለማድረግ የባለስልጣን መስርያቤቱ በተለያዩ ግዚያት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ጥሪ በማድረግ ጉዳቱ ለደረሰባቸው ክልሎች በአይነትና በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡ በዚሁም መሰረት ባለስልጣን መስርያቤቱ በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መኪናን ጨምሮ የተለያዩ የምግብ፣፣መድሃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች በድምሩ ከ 179,520,000 (አንድ መቶ ሰባ ዘጠኝ ሚሊዮን አምስት መቶ ሃያ ሺ ብር) የሚገመት ድጋፎችን ማድረጋቸውን አቶ ጂማ ዲልቦ አክለው ገልጸዋል ፡፡ የአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው የአፋር ክልል ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ፈተናዎች ውስጥ ማለፉን ገልጸው በችግራችን ግዜ ሁሉ የሁሉም ክልሎች እንዲሁም አንዳንድ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በኩል የተደረገላቸውን ድጋፍ አመስግነዋል፡፡ ዛሬም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የተደረገልን ድጋፍ ይህንኑ የሚያመላክትና ኢትዮጵያዊነትንና ወንድማማችነትን የሚያሳይ ነው በማለት በክልሉ በጦርነቱ በደረሰው ከፍተኛ ጉዳትና የተፈናቀለው ማህበረሰብ ቁጥር አንፃር ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡