የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአዳማ ከተማ ፕሮግራሙን አዘጋጅተዋል፡፡ በበዓሉ በክብር እንግድነት የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሙና አህመድ እንደተናገሩት በጎ ፈቃደኝነት ዜጎች ከራስ ወዳድነት እና ፍላጎት ወደጎን ብለው የዘር ስብጥር አስተዳደግና አመለካከት አልያም የድንበር ወሰን ሳያግዳቸው ከቅን ልቦና በመነጨ ያለምንም ክፍያ በራሳቸው ተነሳሽነት ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን እና እውቀታቸውን ተጠቅመው የሰውችን ሰብዓዊ ህይወት ለማሻሻል ማህራዊ ተሳትፎን እና ማህራዊ ትስስርን ለማጠናከር የሚውል በጎ ተግባር ነው፡፡ ሚኒስትር ዴኤታዋ ቀኑን ማክበር ያስፈለገበት ዓብይ ምክንያት ብለው ያነሱት በአሁኑ ወቅት በአገራችን ውስጥ በተፈጥሮአዊና በሰው ሰራሽ ክስተቶች ሳቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችን በመኖራቸው ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ ሁላችንም በጋራ መቆም ይገባናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ሌላው ያነሱት በአገራችን የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ከህዝባች ታሪክ ባህል ወግና እሴቶችን ከማህበራዊ መስተጋብሮች ጋር የተቆራኘ የረጅም ጊዜ ታሪክ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት በአገር ደረጃ በተበጣጠሰ መንገድ ሳይሆን ወጥ እንዲሆን እና የዘርፉን እንቅስቃሴና የወጣቶችን ተሳትፎ ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ብሄራዊ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፖሊሲ እና የወጣቶች የዜግነት አገልግሎት አዋጅ በረቂቅ ደረጃ እየተዘጋጀ መሆኑን በመግለጽ የበጎ ፋቃደኝነት አስተሳሰብ በማህበረሰቡ ዘንድ በማስረጽ ዜጎች በአገልግሎት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪአቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንዳሉት የበጎ ፈቃደኝነት ቀን ከመሪ ቃሉ ስንነሳ በጎ ፈቃደኝነት ለአገር አንድነትና አብሮነት ቁልፍ ሚና እንዳለው የሚገልጽ ነው በማለት በአሁኑ ወቅት አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር እየተደረገ ካለው አኳያ ትልቅ እንድምታ አለው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አክለውም የአገራችን ኢትዮጵያ አንድነትና አብሮነት የሚረጋገጠው በስርዓት ታንጾ ባደገ ቅን ልብ እና በጎ አድራጊነትና አስተዋይ ልቦች ነው በማለት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በእድሜ፣ በፆታ፣ በዘር፣ በሃይማኖት እና በድንበር ሳይገደብ ሰብዓዊ መልክ ብቻ በመከተል የሚከናወን ተግባር መሆኑን አንስተዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአዋጅ 1113/2011 መሰረት በህገ መንግስቱ የተረጋገጠውን የመደራጀት መብት በተሟላ መንገድ በማክበር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህግን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ፤በአገራችን የበጎ አድራጊነትና የበጎ ፈቃደኝነት ባህል በህብረተሰቡ ውስጥ በማስረጽ ፤ድርጅቶች በአገር ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው በማስቻል የተደራጀ ማህበረሰብ በመፍጠር የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት እና የአገራችንን ብልጽግና ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ነው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ሌለዋው ዋና ዳይሬክተሩ ያነሱት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሳይቆራረጥ ተቋማዊ አሰራር ተዘርግቶለት እንዲከናወን ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በመግለጽ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለአገራችን ልማት ፣አንድነት፣ ሰላምና መረጋጋት ቁልፍ ሚና እዳለው በመረዳት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል እና ተቋማ በጋራ መስራት እንደለባቸው አንስተዋል፡፡ የበጎ ፈቃድ አድራጊዎች እና በጎ ፈቃድ ፈላጊዎች ለማገናኘት የሚያስችል /VMSI/ የተባለ የመመዝገቢያ ድህረገጽ ተዘጋጅቶ በዛሬው እለት ተመርቆ ተከፍቷል ፡፡ በመጨረሻም በዚህ ተግባር በጎ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ድርጅቶች የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡