በዓለም ለ31ኛ ጊዜ እንዲሁም በኢትዮጵያ ለ30ኛ ጊዜ “አካታች የፈጠራ የስራና ሽግግራዊ መፍትሄ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ሁለንተናዊ ተደራሽነት” በሚል መሪ ቃል በድሬደዋ አስተዳደር ሚንስትሮች፣ የአስተዳደሩ ከፍተኛ ኃላፊዎች እንዲሁም በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት በከፍተኛ ድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡ ከዋዜማው ጀምሮ በበርካታ ሁነቶች የታጀበው ዓለም ዓቀፉ የአካል ጉዳተኞች ቀን በድምቀት የተከበረ ሲሆን በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ በትብብር እየሰሩ ለሚገኙ አካላትና ለበዓሉ መሳካት አስተዋጽዖ ላበረከቱ የሲቪል ማህበራት እውቅናና ምስጋና ተሰጥቶበታል፡፡ በመክፈቻ መርኃ ግብሩ የተለያዩ ተቋማት አካል ጉዳተኞችን በሚመለከት እየሰሩ ያሉትን ስራ ያቀረቡ ሲሆን በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በኩል አካል ጉዳተኞችን መሰረት አድርገው ለሚቋቋሙ ድርጅቶች ስለሚሰጥ ድጋፍና በኢትዮጵያ ስላለው እንቅስቃሴ እንዲሁም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አካል ጉዳተኞችን በሚመለከት እየሰራቸው ስለሚገኙ ስራዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡

በክብርት ሚንስትር ደኤታ ወ/ሮ አየለች አወያይነት በተካሄደው በዚህ የፓናል ውይይት ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሚያወጣቸው ህጎችና መመሪያዎች ላይ አካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኙ አንስተው በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ለሚሰሩ ድርጅቶች የድጋፍና ክትትል ዴስክ በማደራጀት በልዩ ሁኔታ በእቅድ እየሰራበት እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት የተሰባሰቡና በአስተዳደሩ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች የሚገለገሉባቸው ቁሳቁሶች በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር በኩል ለአስተዳደሩ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ተበርክቷል፡፡ በነበረው መርኃ ግብር የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በተገኙበት ቸሻየር ኢትዮጵያ የተባለ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የተመዘገበ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት በድሬደዋ አስተዳደር እየሰራ ያለው ስራ ተጎብኝቷል፡፡