የክልሉ ምክትል ፕረዝዳንት አቶ ኢብራሂም ዑስማን በጉባኤው ባስተላለፉት መልዕክት የሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች ህብረተሰቡን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዬች ላይ ያለው ግንዛቤ እንዲዳብር ማድረግን ጨምሮ በሚሰሯቸው ሌሎች ዘርፈብዙ ስራዎች ለሃገር ሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ እሙን ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ በባለፈው ዓመት በክልላችን አስከፊ ድርቅ መከሰቱን ተከትሎ ድርቁን ለማቋቋም በተደረገው ርብርብ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ በማቅረብና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የጉዳቱን መጠን ለመቀነስ ያደረጉትን አስተዋጽኦ በመጥቀስ በድርቁ ወቅት ላሳዩት አጋርነትና ድጋፍ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ የሶማሌ ክልልም የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶችን ያላሳተፈ እድገት እንዲሁም የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚፈለገውን ውጤት እንደማያመጣ ይገነዘባል በማለት ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች በእኩልነት ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘላቂነት ያለው ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በአግባቡ ሚናቸውን መወጣት የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ እንዲኖር በቁርጠኝነት ይሰራል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፍቃዱ ጸጋ በበኩላቸው መንግስት በዘርፉ ለውጥ እንዲመጣ የህግ ማሻሻያዎችን ብሎም የአመራር ለውጥ በማድረግ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ አስመዝግቧል ያሉ ሲሆን ሲሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም በሃገሪቱ የልማትና የመልካም አስተዳድር ጉዳዬች የማይተካ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡ አያይዘውም ለዚህ ሃገር ፈተና የሆነውን የመልካም አስተዳድር ፈተና ዜጎች ተጋላጭ እንዳይሆኑ በማንቃት ረገድም ትልቅ ሚና አላቸው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የሲቪል ማበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ባስለተላለፉት መልዕክት ይህ የጋራ ጉባኤ በዋናነት የሲቪል ማኅበረሰብ ዘርፉን ለማሳደግ እና የተሻለ ድጋፍና ክትትል ሥርዓት ለመዘርጋት፣ የዜጎች የመደራጀት መብት ለማረጋገጥ የሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል መንግስታት በቅንጅት መስራት፣ በተቋማችንና በፌደራልና በክልል ተቋማት መካከል ዘመናዊና ፈጣን የመረጃ ልውውጥ መፍጠር፣ አገር በቀል ድርጅቶችን በማጠናከር በዘርፉ የሚደረገው አስተዋፅኦ ዘላቂና አስተማማኝ እንዲሆን ማስቻል፣ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በማከናወን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በልማትና በዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ያላቸውን ሚና ማጎልበት እና ድርጅቶች የሚሰሯቸው የልማት ስራዎች ከመንግስት የልማት ዕቅዶች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል፡፡
በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ለተፈናቀሉ የማህበረሰብ ክፍሎች በሶስት ዙር በተደረገ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር በአጠቃላይ ከአምስት መቶ አርባ አራት ሚሊየን ብር በላይ በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉንም በንግግራቸው አካተው ገልጸዋል፡፡ ከአምስተኛው ጉባኤ በኋላ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ያጋጠሙ ችግሮችና የወደፊት የትኩረት አቅጣጫን የያዘ ሪፖርት በምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል፡፡