የፍትህ ሚንስቴር ሚንስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በተገኙበት በደቡብ አፍሪካ ስለተደረገው ስምምነት ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ገለጻ ተደርጓል፡፡ ስምምነቱ ምን ምን ጉዳዮችን እንዳካተተ ፣ በቀጣይ ስለሚወሰዱ ርምጃዎች እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ስለሚገባቸው አስተዋጽዖ ሰፊ ገለጻ ተሰጥቷል፡፡ በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በስምምነቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ቅስቀሳዎችን ወደጎን በመተው በስምምነቱ መሰረት ተግባራዊ እንዲሆን በጎ ተጽዕኖ ማድረግ ብሎም በጦርነቱ የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎችንና የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ በማቋቋም ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው ዶ/ር ጌዲዮን ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም መንግስት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያደርገው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለሀገራዊ መግባባትና ለዘላቂ ሰላም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ከሰላምና ከሀገራዊ ምክክር ጋር በተያያዘ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው የተጠቀሰ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ከጊዜ ወደጊዜ ስር እየሰደደ የመጣውን ሙስና በመረጃና በማስረጃ በመሞገትና በማጋለጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡ የመድረኩ ተሳታፊዎች መንግስት እየወሰደ ያለውን ርምጃ አድንቀው የሲቪል ማህበረሰብ ዘርፉ ለስምምነቱ መሳካት የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡