የኢትዮጵያ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን የልማት ድርጅት ከኮምፓሽን ኢንተርናሽናል ባገኘው የ20.6 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ በጦርነቱ ጉዳት በደረሰባቸው የሰሜን ሸዋ፣ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች 18 ትምህርት ቤቶችን መልሶ የማቋቋም ፕሮጀክት በትግበራ ላይ እንደሚገኝ የድርጅቱ ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ታገለ ማቴዎስ ገለጹ፡፡ የድርጅቱ ስራስኪያጅ አቶ ታገለ ማቴዎስ እንደገለጹት በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን አንስተው ድጋፉ በዋናነት ኮምፒውተር፣ የተማሪዎች መቀመጫ ወንበር፣ ፎቶ ኮፒ ማሽን፣ ፕሪንተር እና የፈተና ማባዣ ማሽኖችን ያካተተ ነው ያሉ ሲሆን በሸዋ ሮቢት፣ በደሴ፣ በኩታበር፣ በሀይቅ፣ በወልዲያ፣ በቆቦ ከተሞች የተማሪ መቀመጫ ወንበሮች ደርሰዋል ብለዋል፡፡ ቀሪ ስራዎችም በሚቀጥሉት ሳምንታት እንደሚጠናቀቁ አክለው አብራርተዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ የኃይማኖት ተቋማት ለረጅም ዘመናት ከሃይማኖታዊ ተግባራቶቻቸው ጎን ለጎን ኅብረተሰቡን ለማገዝ በልማት ስራዎች ላይ ሲሳተፉ ቆይተዋል ያሉ ሲሆን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እንዲህ ያለውን ተግባር በእጅጉ እንደሚያበረታታ ገልጸዋል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር የተለያዩ ድጋፎችን ለተጎጂዎች እያደረሰ እንደሚገኝ ጠቅሰው የኢትዮጵያ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን የልማት ድርጅት ከኮምፓሽን ኢንተርናሽናል ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ 18 ትምህርት ቤቶችን መልሶ በማቋቋም እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕይወት ብርሃን ቤተክርስቲያን የልማት ድርጅት ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ የልማት ስራዎችንና የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፎችን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከ140 ሚሊዮን በላይ አመታዊ በጀት በመመደብ ከ10 አጋር ድርጅቶች ጋር በዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በፕሮጀክት ገለጻው ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦን ጨምሮ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ እና ፋይናንስ ቢሮ ተወካዮች እንዲሁም የኮምፓሽን ኢትዮጵያ ተወካይ ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡