በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን አስተባባሪነት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን እንዲሁም አልባሳትን በደብረብርሃን ከተማ ተጠልለው ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ ተደርጓል፡፡ በሶስተኛው ዙር የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሰብዓዊ ድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ለበርካታ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተለያዩ የጸጥታ መደፍረስ ምክንያቶች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ መተላለፉ የሚታወስ ነው፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ኤስ አይ ኤም ኢትዮጵያ (SIM-Ethiopia) ከተባለ የውጪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ጋር በመተባበር ከአንድ ሚልየን ብር በላይ ግማታዊ ዋጋ ያላቸው የምግብ፣ የአልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል፡፡ በድጋፉ ወቅት ንግግር ያደረጉት የሲቪል ማህበረሰብ ድጅቶች ባለስልጣን የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በፍቃዱ በሀገሪቱ ክፍሎች በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው ለሚገኙ ዜጎች ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር የተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፎችን ሲያቀርብ መቆየቱን አውስተው ካሁን በፊት ወደዚህ አካባቢ በመምጣት በገባንው ቃል መሰረት ለዚሁ ዓላማ ከተቋቋመ ኮሚቴ ጋር በመነጋገር ድጋፉን ይዘን መጥተናል ብለዋል፡፡
አክለውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር በተለያዩ የመጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አንስተው ተፈናቃዮች ወደቀያቸው ተመልሰው የተረጋጋ ኑሮ እስኪጀምሩ ድረስ ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አክለው ገልጸዋል፡፡ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ ድባቤ፤ በወይንሸት መጠለያ ጣቢያ ከ6800 በላይ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ አንስተው ከወር በፊት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላዎች በገቡት ቃል መሰረት ቃላቸውን ጠብቀው ከኤስ አይ ኤም ኢትዮጵያ (SIM-Ethiopia) ጋር በመሆን ድጋፉን ይዘው በመምጣታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በመንግስትና በተለያዩ ድጋፍ አድራጊ አካላት ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም በቂ አይደልም ያሉት አቶ ግርማ በሁሉም የመጠለያ ጣቢያዎች የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ እጥረት ያለ በመሆኑ ይህ ጊዜ እስኪያልፍ እንድንረዳዳ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ ብለዋል፡፡ ኤስ አይ ኤም ኢትዮጵያ (SIM-Ethiopia) በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተመዝግቦ በተለያዩ የሰብዓዊ ድጋፍና ልማት ስራዎች ላይ የተሰማራ የውጪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሲሆን በኦሮሚያ፣በደቡብና በአማራ ክልል በተለይም በባህርዳርና በእንጅባራ፣ የተለያዩ የልማት ፕሮጅክቶችን እየሰራ ይገኛል፡፡ የኤስ አይ ኤም ኢትዮጵያ (SIM-Ethiopia) ሲኒየር ሚኒስትሪ ማናጀር የሆኑት አቶ ነብዩ ኃይሌ እዚህ ደብረብርሃን ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተፈናቃይ ያለ መሆኑን ስንሰማ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በመነጋገር የስንዴ ዱቄትና የምግብ ዘይት ድጋፍ አድርገናል ያሉ ሲሆን ማህበረሰባችን ከገጠመው ችግር እስኪወጣ ድረስ አቅም በፈቀደ መጠን ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡