መሰረቱን እንግሊዝ አገር ያደረገው ችልድረንስ ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን (children’s investment fund foundation (CIFF UK)) የተባለ የውጪ ድርጅት የአፍሪካ ክልላዊ ቢሮውን (The CIFF UK Africa Regional office) በአዲስ አበባ ለመክፈት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ከሲቪል መማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር ተፈራርሟል፡፡ በስምምነቱ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላን ጨምሮ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎችና የCIFF የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ ስምምነቱን የተፈራረሙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አጠቃላይ ህጋዊና ተቋማዊ ማዕቀፍ መሻሻሉንና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የልማት አጋር እንደሆኑ የሚያሳይ የህግና የፖሊሲ ማዕቀፍ መኖሩን አንስተው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይህን ለማስፈጸም ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡ የሚያሰራና ምቹ የሆነ የስራ ሁኔታ በመፈጠሩ የውጪ ድርጅቶችም ሆኑ ሀገር በቀል ድርጅቶች ከጊዜ ወደጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ በርካታ የውጪ ድርጅቶች ክልላዊ ቢሯቸውን (Regional office) በኢትዮጵያ እየከፈቱ እንደሚገኙና የልማት አጋሮቸቻችን እየሆኑ እንደሆነ አንስተው CIFF UKም የዚሁ መሻሻል ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አቶ ፋሲካው በንግግራቸው ድርጅቶችን ህግ አውጥቶ ከማስተዳደር ባሻገር እንደ CIFF UK ያሉ የተለየ ባህሪ ያላቸውን ድርጅቶች መፍትሄ የሚሰጥ አሰራር መዘርጋት ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን ይህ የመግባቢያ ስምምነት የተፈረመው ድርጅቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለማስተዳደር እንዲያመችና ድርጅቱም በተሻለ ሁኔታ መንቀሳቀስ እንዲችል እድል የሚሰጥ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በአፍሪካም፣ በእሲያም ሆነ በተለያዩ አህጉራት የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው አህጉር አቀፍ እና ክልል አቀፍ ቢሮዎችን ቢከፍቱ መንግስት እጁን ዘርግቶ እንደሚቀበላቸው ያነሱት አቶ ፋሲካው ለዚህም የተሻለና ሊያሰራ የሚችል የህግ ማዕቀፍና ፖሊሲ ያለ መሆኑን በመጠቆም አለም አቀፍ ድርጅቶች አህጉር አቀፍ ቢሮዎቻቸውን በኢትዮጵያ እንዲከፍቱ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
ችልድረንስ ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን (children’s investment fund foundation (CIFF UK)) በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2020 በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተመዝግቦ በእናቶችና ህጻናት ጤና፣ በቤተሰብ ምጣኔና በአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም በስነ ምግብ ላይ የሚሰራ የውጪ ድርጅት ሲሆን ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ የሚከፍት ይሆናል፡፡ድርጅቱ በዓመት ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በመላው ዓለም ኢንቨስት እያደረገ የሚገኝ ድርጅት ሲሆን በኢትዮጵያ ክልላዊ ቢሮውን በመክፈቱ ከ230 ሚሊዮን ዶላር በላይ በኢትዮጵያ ኢንቨስት የሚያደርግ ይሆናል፡፡ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከተከሰተው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘም በዩኒሴፍ በኩል ከ15-20 ሚሊዮን የሚደርስ ድጋፍ እንግሊዝ በሚገኘው ዋና ቢሮው አማካኝነት ድጋፍ ማድረጉንና በቅርቡ ለተጎጂዎች በዩኒሴፍ በኩል እንደሚደርስ የድርጅቱ  የአፍሪካና የኢትዮጵያ ተወካይ ዶ/ር አብርሃም አስማረ ገልጸዋል፡፡