በስነስርዓቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደተናገሩት ድርጅቱ በበጎ ፈቃደኛና ልበ ብሩሃን በሆኑ ወጣቶች ከዘሬ ሃያ አምስት ዓመታት በፊት ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ የማህበረሰብ ክፍሎችን መደገፍ ዓላማ አድርጎ “ጣምራ የፀረ-ኤድስ ክበብ” በሚል ስያሜ የተቋቋመ እና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ተመዝግቦ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም አፍላ ወጣቶቹ በወቅቱ የነበራቸውን እምቅ የኪነ-ጥበብ ተሰጥዖ እንደ አብይ መሳሪያ ተጠቅመው በትምህርት ቤቶች፣ በስፖርት ሜዳዎች በከተማ ጎዳናዎች እና በየመንደሩ እየተዘዋወሩ ስለ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ በሽታ አስከፊነት ህብረተሰቡን በማስተማርና የታመሙትን በመንከባከብ እንቅስቃሴያቸውን መጀመራቸውን አስታውሰው ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች የጤናና ማህበራዊ ጉዳዮችም በማስፋት ህብረተሰቡን በተለይም ሴቶችን፣ ወጣቶችንና አቅመ ደካሞችን ትኩረት አድርጎ መስራቱ በአብነትነት የሚያስጠቅሰውና የሚያስመሰግነው ጉዳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም የምስረታ ባህላቸውን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ጣምራ ለማህበራዊ ልማት ወጣቶች ማህበር በ25 ዓመታት ውስጥ ያሳካቸውን ዓላማዎች የበለጠ በማስፋት፣የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ከዚህ የተሻለ ስራ እንደምትሰሩ ተስፋ አደርጋለሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::