በማላዊ የፆታ፣ የማህበረሰብ ልማት እና ማህበራዊ ደህንነት ሚኒስቴር ተወካይ በሆኑት ወ/ሮ ሮዝሊን የተመራ ልዑክ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በመገኘት የልምድ ልውውጥ አድርጓል፡፡ የልምድ ልውውጡን ያደረጉት በማላዊ መንግስት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የስራ ኃላፊዎች ሲሆኑ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በመገኘት በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ታሪክ፣ እንቅስቃሴ እና ተቋሙ እያከናወነ ስላለው ተግባር በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በማብራሪያቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ምህዳሩን ለማስፋት በርካታ ተግባራት መከናወኑን በማንሳት ባለፉት አራት አመታት ብቻ ከ2500 በላይ አዲስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንደተመዘገቡ ፣ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ዘርፉ ለሀገር የሚጠበቅበትን እንዲያበረክት የተለያዩ የህግ ማሻሻያዎችን ማድረጉን፣መምሪያዎችንና ማኗሎችን በማዘጋጀት ግልጽና ተገማች የሆነ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡ ተቋማዊ የሪፎርም ስራዎች፣የበጎ ፈቃድና በጎ አድራጊነትን በማህበረሰቡ ውስጥ ለማስረጽ የተከናወኑ ስራዎች፣ቴክኖሎጂን ከመጠቀም አንጻር፣ከፈንድ አስተዳድር አንጻር የተከናወኑ ተግባራት፣የአጋርነት እና ትብብር ስራዎች፣ከድርቅና ከሰብዓዊ ድጋፍ አንጻር ድርጅቶችን በማስተባበር የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
በማላዊ የፆታ፣ የማህበረሰብ ልማት እና ማህበራዊ ደህንነት ሚኒስቴር ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ሮዝሊን በበኩላቸው በማላዊ ያለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አደረጃጀት ኢትዮጵያ ካለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አደረጃጀት የተለየ እንደሆነ አንስተዋል፡፡ አያይዘውም በማላዊ ከባለስልጣነ መስሪያ ቤቱ ጋር አቻ የሆነ ኃላፊነት የተሰጠው መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የሚባል መሆኑን በማንሳት በዚህ ተቋም ውስጥ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የመመዝገብና የመቆጣጠር ስራዎችን እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡ በማላዊ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን የኮርፖሬት ሰርቪስ ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ሊንዳ ብሪጌት በበኩላቸው ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በጣም ጠቃሚ የሆኑ ልምዶችን ማግኘት መቻላቸውን አንስተው ወደተቋማቸው ተመልሰው በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያገኙትን ተመክሮ ተግባር ላይ እንደሚያውሉት አብራርተዋል፡፡