በድልድል መመሪያ ቁጥር 859/2014 ዙሪያ ስልጠና በተሰጠበት ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደገለጹት ተቋሙ በባለፉት ሶስት ዓመታት በሪፎርም ውስጥ ማለፉን በማንሳት ለአንድ ተቋም ውጤታማነት ሃሳብ፣መዋቅር እና የሰው ሃይል መሰረታዊ ጉዳዬች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ የትልልቅ ተቋማት ጅማሮ ሃሳብ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ እኛ እንደተቋም የጠራ ሃሳብ አለን ሃሳብን ወደ ተግባር ለመለወጥ ደግሞ ግልጽ የሆነ የማህበረሰቡን የመደራጀት መብት እና የማህበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መዋቅር ጸድቆ መጥቷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ሃሳብ እና መዋቅር ውጤታማ እንዲሆን ደግሞ የሰው ሃይል ወሳኝ ነው፤ ይህ የድልድል መመሪያም ለሁሉም ኮሚቴዎችና የተቋሙ ሰራተኞች ግንዛቤ በማስያዝ በእውቀት፣ክህሎትና በስነምግባር የታነጸ የሰው ሃይል እና ሁልግዜ ለመለወጥ፣ለመማር እና አዳዲስ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም ዝግጁ የሆነ የሰው ሃይል በተቋሙ እንዲኖር ይሰራል ብለዋል፡፡
አዲሱ ድልድል እንደሃገር ለየት ያሉ ጉዳዬች እንዳሉት በማንሳት እንደተቋምም በሪፎርም ውስጥ እንደቆየ ተቋም ይህ አዲስ ድልድል የተቋሙን ዓላማ ወደፊት የሚራምድ እና ወደ ሌላ ከፍታ የሚወስድ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በመጨረሻም የተቋሙን ርዕይ መሰረት ያደረገ ድልድል እንደሚፈጸም አምናለሁ በማለት ከመመሪያው በተጨማሪ የሃገሪቱን የ10 ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ ታሳቢ ይደረጋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡