የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ጸድቆ ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ለአካል ጉዳተኞችና ልዩ ትኩረት በሚሹ ዘርፎች ላይ ለሚሰሩ ድርጅቶች ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ በተቋሙ ለሚሰሩ የምዝገባ፣ ክትትልና ድጋፍ ባለሙያዎች በአካል ጉዳተኞች መብት እና አሳታፊነት ዙሪያ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሄራዊ ማህበር ጋር በመሆን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ በስልጠናው መክፈቻ ላይ የባለስልጣን መስሪያቤቱ የምዝገባ፣ ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተሾመ ወርቁ ባስተላለፉት መልዕክት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለአካል ጉዳተኞችና ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ለሚሰሩ፤ ሴቶች ፣ ህጻናት፣ አረጋውያን ላይ ለሚሰሩ እና መሰል ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች ቅድሚያ በመስጠት መርህ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አደረጃጀቱን እየከለሰ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ተሾመ ወርቁ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አዲሱ አደረጃጀት የአካል ጉዳተኞች ዴስክ እንደሚቋቋም አንስተው ተቋሙ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማቀላጠፍና በተለይም አካል ጉዳተኞችን በሚመለከት ልዩ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ያስችለናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሄራዊ ማህበር ዳይሬክተር የሆኑት ወ/ሮ ድባቤ እንዳሉት የቀድሞው አዋጅ ተነስቶ አዲሱ አዋጅ 1113/11 ከወጣ በኋላ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እየሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመው ለዚህም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱን አመስግነዋል፡፡ አያይዘውም ድርጅቶች የፕሮጀክት ቅድመ ጥናት ሲያቀርቡ የአካል ጉዳተኛ ሴቶችና ህጻናትን ያካተተ መሆን ይኖርበታል ያሉት ወ/ሮ ድባቤ ስልጠናው እስከዛሬ የተገመገሙ ፕሮጀክቶች እይታዎቻችን አካል ጉዳተኛ ተኮር ናቸው ወይ የሚለውን በመመልከት በክትትልና ግምገማ ስርዓታችን የአካል ጉተኞችን መብትና ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ የሚደረግ ነው ወይ የሚለውን ለመፈተሸ ያግዛል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ሴቶች ብሄራዊ ማህበር በ1995 ዓ.ም በ8 አካል ጉዳተኛ ሴቶች አማካኝነት የተመሰረተ ሲሆን በአሁን ጊዜ 555 በላይ አካል ጉዳተኛ ሴቶች አባላት እንዳሉት በማህበሩ ዳይሬክተር በወ/ሮ ድባቤ ተጠቅሷል፡፡