“እኛ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አደጋውን ለመቀነስ ድርሻ አለን` በሚል መሪ ቃል በ03/13/2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 1፡30 ሆኖ መነሻውን መስቀል አደባባይ ፤ መድረሻውን ካዛንችስ ያደረገ የእግር ጉዞ በማድረግና በፓናል ውይይት የመንገድ ደህንነት ቀን ተከብሮ ውሏል፡፡ በመርኃ ግብሩ ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ በዕለቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ባስተላለፉት መልዕክት የመንገድ ደህንነት ቀን ከሰላም ቀን ጋር በአንድ ላይ መዋሉ ድርብ በዓል ነው ፤ስለመንገድ ደህንነት ሲነሳ ህብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባቱ መረጋገጥ አለበት፤ ስለዚህ እነዚህን ሁለት በዓላት ስናከብር ትልልቅ መልዕክቶችን እያስተላለፍን ነው ብለዋል፡፡ በመንገድ ደህንነት ዙሪያ የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥቂት ቢሆኑም ተነሳሽነታቸው ትልቅ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በዚህ አይነት ተግባር ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችንም ሆነ ግለሰቦችን ማበረታታትና ማገዝ ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በመንገድ ደህንነት ላይ የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የሚያበረታታ መሆኑንና ከመንገድ ደህንነትና መድኅን ፈንድ አገልግሎት ጋር በጋራ እንደሚሰራ አክለው ገልጸዋል፡፡




በፓናል ውይይቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው በመንገድ ደህንነት ችግር በርካታ የሰው ህይወት፣ የአካል ጉዳትና የሀገር ንብረት መውደሙን አንስተው ችግሩ ከእለት እለት እየጨመረና እየሰፋ መምጣቱን አንስተዋል፡፡ ጉዳዩ ሀገራዊ ጉዳይ በመሆኑ የሁሉንም ርብርብ ይሻል ያሉት ምክተል ዋና ዳይሬክተሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በመንገድ ደህንነት ጉዳይ ላይ በስፋት ሊሰሩበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ አክለውም ግንዛቤ በመፍጠር፣ በፖሊሲና በህግ ማዕቀፍ መመራት መተግበር፤ በጥናትና ምርምር ማገዝ እና ዘላቂና ቀጣይነት ያለው ስራ ማከናወን ችግሩን ለመቅረፍ ያስችላል ያሉ ሲሆን በየዘርፉ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ውጤታማ ያደርጋል ብለዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በርካታ ስራዎችን እየሰራ ሲገኝ ከጳጉሜ እስከ ጳጉሜ እንደርሳለን በሚል የመግባቢያ ሰነድ ከቀድሞው የትራንስፖርት ሚንስቴርና ከመንገድ ደህንነት ማህበር ጋር መፈረሙ የሚታወስ ሲሆን በተለያዩ የመንገድ ደህንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ መርኃ ግብሮች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡