ይህ የተገለፀው የሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የ2014 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ በሚያቀርብበት ወቅት ነው፡፡
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንዳሉት ከአገራችን ፈተናዎች መካከል የዴሞክራሲ ባህል አለመጎልበት፣ ድህነትና የሰላም እጦት መሆኑን በመግለጽ በተለይም በአሸባሪው ህወሓት ቡድን የተከፈተው ተደጋጋሚ ጦርነት ለአገራዊ አንድነት ትልቁ ፈተና ሆኖ ይገኘል ሲሉ ገልፀዋል፡፡ በመንግስት በኩል የተደረገው የተናጥል የተኩስ አቁም ስምምነት በመደፍጠጥ ለሰላም የተዘረጉ እጆችን ባለመቀበል ቡድኑ ከውጪ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር ኢትዮጵያን ለመበታተን ለሶስተኛ ጊዜ የከፈተብን ጦርነት አሁንም ለሰላማዊ ዜጎች ሞት መፈናቀልና ስደት መዳረጉን አንስተዋል፡፡ መንግስት አሁንም ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ይህ ቡድን የወረረውን አካባቢ በመልቀቅ ወደ ሰላም እንዲመለስና ችግሮችን በውይይት ብቻ እንዲፈቱ አሁንም ተስፋ ባለመቁረጥ ጥረት እንያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ሌላው ያነሱት ሀገራዊ አንድነታችንን በማጠንከር ፊታችንን ወደ ልማት ለማዞር ከጦርነት አዙሪት ውስጥ መውጣት አለብን፤ በጦርነት ውስጥ ሆኖ ዘላቂ ልማት ማሰብ አይቻልም፤ በድህነት ውስጥ ያለችን ሀገር በጦርነት አዙሪት ውስጥ ማቆየት ለኢትዮጵያ አይገባትም፣ አገራችን በብዙ መከራዎች ውስጥ ያለፈች አገር ናት፤ ያጋጠሟት ፈተናዎችና መከራዎች ሊበታትኗት ባይችሉም በርካታ ጠባሳዎችን ጥለዋል፡፡ ይህን የታሪክ ገጽ ለማረምና ለቀጣዩ ትውልድ ሰላምን፣ ልማትንና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ማውረስ እንዲቻል ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለይም የሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡
የኢፌድሪ ህገ መንግስ አንቀጽ 12 የመንግስት አሰራር ለህዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት በሚል በደነገገው መሰረት የሲቪል ማበረሰብ ድርጅቶች ባለስጣን የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ክንውን ሪፖርት እንዲሁም የ2015 በጀት ዓመት እቅድ ለተገልጋዮች ማቅረብ የመድረኩ ዋና ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባስልጣን መስሪያ ቤቱ በ2014 በጀት ዓመት ትኩረት ያደረገባቸው የረፎርም ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል፣የተገልጋዮችን እርካታ ማሳደግ፣አገልግሎት አሰጣጡን ዲጂታላይዝ ማድረግ፣የበጎ ፈቃደኝነትን ባህልና እንቅስቃሴ ማበረታታት፣ የበጎ ፈቃደኝነትን በተመለከተ የስርፀት ስራ መስራት ድርጅተቶች ግልፀኝነትና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ የውስጥ አስተዳደር እና የራስ አስተዳደር ስርዓት እንዲኖራቸው ድጋፍ መስጠትና ተፈጻሚነታቸውን መከታተል እንዲሁም ድርጅቶች ስራዎቻቸውን በህግ አግባብ ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ዋና ስራዎች መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም ዋና ዳይሬክተሩ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን በ2014 በጀት ዓመት በርካታ ስራዎች የተሰሩ መሆኑን ገልጸው በዋናት በተቋሙ የሚሰጡ 48 አገልግሎቶችን በመለየት የኢ-ሰርቪስ አገ ልግሎቶችን መስጠት መጀመሩን አንስተዋል፡፡ በ2014 በጀት ዓመት የተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጥ እርካታ 91.34% ማደጉን ተከትሎ ተቋማችን በሀገር አቀፍ ደረጃ የአገልግሎት ጥራት ሽልማት እጩ ተወዳዳሪ ለመሆን ችሏል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የመደራጀት መብት በተሟላ ሁኔታ መረጋገጥ መቻሉ እና የሲቪክ ምዕዳሩ መስፋቱ እንደተጠበቀ ሆኖ አዋጁን በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ 17 የሚሆኑ መመሪያዎች በማዘጋጀት 8ቱ በቦርድ መጽደቃቸውን ጠቅሰው በ2014 በጀት አመት 545 የሚሆኑ ድርጅቶች ተመዝግበው ስርተፍኬት መውሰዳቸውን እንዲሁም ክትትልና ድጋፍን በተመለከተ 1781 ድርጅቶች የዴስክ ኦዲት ከ297 ድርጅቶችን የመስክ ክትትል የተደረገላቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡ አያይዘውም በጥንካሬ ሊታዩ ከሚችሉት መካከል ብለው የጠቀሱት ከክሎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው ጉባኤ አማካኝነት ለክልሎች ሞዴል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መነሻ ህግ ተዘጋጅቶ ውይይት መደረጉን፣ ክልሎች ህግ እንዲያወጡ ድጋፍ መደረጉ፣የመረጃ ስርዓታችንን ለማጠንከር ጥረት መደረጉ፣ የበጎ ፈቃድ አተገባበር ማንዋል መዘጋጀቱ፣የአገልግሎት አሰጣጣችን እየተሻሻለ መምጣቱ፣ የማማክርት ጉባኤ መቋቋሙ፣ በፀደቁ መመሪያዎች ላይ ስልጠናችን መስጠቱ ሌሎችም በጥንካሬ የሚገለፁ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ በውስንነት የታዩ ጉዳዩች ብለው ያነሱት ዳግም ያልተመዘገቡ 1723 ድርጅቶች በሚኒስተሮች ም/ቤት በፀደቀው ደንብ 514/2014 መሰረት በድጋሚ እንዲመዘገቡ የተፈቀደ ቢሆነም የተመዘገቡት ቁጥራቸው አነስተኛ መሆኑ አንዳንድ ስራዎች በእቅድ ተይዘው አለመፈጻማቸውን አንስተዋል፡፡ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ የ2014 በጀት ዓመት ዝርዝር አፈጻጸሞችን እንዲሁም ወ/ሮ ቃልኪዳን መንግስቴ የእቅድ በጀትና ለውጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የ2015 በጀት ዓመት እቅድን አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል::