የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን “አረንጓዴ አሻራችን ለትውልዳችን” በሚል መሪ ቃል ከፍትህ ሚንስቴር ተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር አካሄደ፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በሰሜን ሸዋ ዞን አሳግርት ወረዳ ታሞ ቀበሌ ከሶስት ሺህ በላይ ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችን የፍትህ ሚንስቴር ሚንስትር ደዔታ አቶ አለም አንተ አግደውና የሰሜን ሸዋ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ክላል ሳህለማሪያም እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በተገኙበት አከናውኗል፡፡
የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ክላል ሳህለማሪያም በአረንጓዴ አሻራው መርኃ ግብር ላይ የተሳተፉትን ሁሉ እንኳን ደህና መጣችሁ ካሉ በኋላ ዞኑ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በዞኑ ከጊዜ ወደ የማልማት ብቻ ሳይሆን የማጸደቅ ስራ እያደገ መምጣቱን አንስተው በአሁን ጊዜ በአንድ ቀን የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ብቻ ወደ 48.6 ሚሊዮን የሚጠጉ ችግኞችን መትከል መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዞኑ ከሁለት መቶ ሰባ ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ ከ180 ሚሊየን ችግኞቸ መተከሉን ምክትል ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡
የፍትህ ሚኒስቴር ሚንስትር ደዔታው አቶ አለም አንተ አግደው በበኩላቸው ችግኝ ከመትከል ባሻገር አብሮ ተባብሮ ለማደግ ያለንን ፍላጎት ለመግለጽና ድጋፋችንን እንዲሁም ከወገናችን ጋር አብረን መሆናችንን ለማሳየት ጭምር መጥተናል ያሉ ሲሆን የአካባቢው ምርታማነት እንዲቀጥልና ለትውልድ እንዲሸጋገር ከተፈለገ ሁሉም አሻራውን ማኖር አለበት ብለዋል፡፡ በቀበሌው የተጀመረው ስራ ትልቅ ነው እኛ ደግሞ ዛሬ እዚህ የተገኘነው ይህንን ተግባር ለመደገፍ ነው በማለት ሚንስትር ዴኤታው አክለው ገልጸዋል፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው ችግኝ መትከል በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አንስተው ከ4 ዓመት በፊት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር እያደገና ባህል እየሆነ መምጣቱን አንስተዋል፡፡
ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብ እንደሚገባ ያነሱት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ካሁን በፊት በዘመቻ ይደረግ የነበረው አሁን ግን አመቱን ሙሉ፤ ክረምት ደግሞ በልዩ ሁኔታ እየተሰራ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ በችግኝ ተከላ መርኃ ግብሩ ላይ የታሞ ቀበሌ ነዋሪዎችን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራልና የክልል እንዲሁም የዞን የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡