የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በመንግስት የተቋቋመው ኢንተር ሚኒስትሪያል ታስክ ፎርስ (inter-ministerial task force) እየወሰዳቸው ስላላቸው ርምጃዎች ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር እየተወያየ ይገኛል፡፡ የውይይቱ ዓላማ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት ተፈጸሙ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለማረም መንግስተ የወሰዳቸውን ርምጃዎች ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለማሳወቅ ነው፡፡ በውይይቱ መክፈቻ ላይ የተገኙት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ መንግስት ከሰብዓዊ መብት ጋር የተያያዙ ጥብቅ ርምጃዎችን ወስዷል ያሉ ሲሆን እነዚህ እርምጃዎች ምን ያህል አጥጋቢ ናቸው በተለይ ከሰብዓዊ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ ለወሰዳጀው አዎንታዊ ርምጃዎች የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምን አይነት እይታ አላቸው የሚለውን ለማወቅና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ በጉዳዩ ላይ ሀሳቡን መግለጽ እንዲችል ተከታታይ መድረኮች እየተዘጋጁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በርካታ ኃላፊነቶች አሉበት ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ በተለይም ማህበረሰቡን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሚደርስበት ጥቃት መከላከልና መጠበቅ እንዲሁም ጥፋት አድራሾችን ለህግ በማቅረብ ሂደት ውስጥ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰሜኑ ጦርነት ወቅት በርካታ ድጋፎችን ማድረጋቸውን አንስተው ነገር ግን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ችግር ከመከሰቱ በፊት የነበራቸው እንቅስቃሴ ደካማ እንደነበር አውስተዋል፡: አያይዘውም አቅም ያለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እየተፈጠሩ መሆኑን ጠቁመው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድምጽ በሁሉም ዘርፍ መሰማት አለበት ያሉ ሲሆን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለዚህ መሳካት ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ የኢንተር ሚኒስትሪያል ታስክ ፎርስ (inter ministrial task force) ኃላፊ ዶ/ር ታደሰ በበኩላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንደማንነኛውም የሚመለከተው አካል መንግስት የሚወስዳቸውን ርምጃዎች የማወቅ፣ የመረዳትና የራሱን አበርክቶ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት በመረዳት መድረኩ እንደተዘጋጀ ጠቁመዋል፡፡

የውይይት መድረኩን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እና  የኢንተር ሚኒስትሪያል ታስክ ፎርስ ኃላፊው ዶ/ር ታደሰ መርተውታል፡፡