ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት የበጎ ፈቃድና በጎ አድራጊነትን ባህል በህብረተሰቡ ዘንድ ባህል ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ መነሻነት በባስልጣን መስሪያ ቤቱ ለሚገኙ ሰራተኞች በሁለት ዙር የሚሰጠውን ስልጠና ዛሬ ጀምሯል፡፡ ስልጠናው ትኩረቱን ያደረገው በበጎ ፈቃድ ይዘት፣ በማህበራዊ በጎነትና በማህበራዊ ተጠያቂነት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ሲሆን በሁለት ዙር ለሁለት ቀናት የሚሰጥ ይሆናል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የዋና ዳይሬክተር አማካሪ አቶ ተስፋዬ ሺፈራው እንዳሉት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣንና ተግባር አንዱ የበጎ ፈቃድ ባህልን በማኅበረሰቡ ውስጥ ማዳበርና ማጎልበት ነው ፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በቀጣይ ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ የተቋሙ ሰራተኞች በቂ ግንዛቤና መረዳት ሊኖራቸው ይገባል ያሉ ሲሆን በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የበጎ ፈቃድና ፈንድ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በኩል የተቋሙ ሰራተኞች በበርካታ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም በአረንጓዴ አሻራ በርካታ ችግኞች መተከላቸው፣ የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስ መቻሉን እንዲሁም የዘማች ቤተሰቦችን ሰብል በመሰብሰብ በርካታ ስራዎችን በመስራት ማህበረሰቡ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን ከመደበኛ ስራው በተጨማሪ እንዲለማመድ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል በማለት ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ በመጪው ክረምትም ትልቅ ንቅናቄ በመፍጠር በርካታ ችግኞችን ለመትከል ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አንስተው እንደሀገር ወደ 20 ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እቅድ እንደተያዘ አንስተዋል፡፡ የበጎ ፈቃድ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ወደተግባር እንዲገባ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡