የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በሰባት ረቂቅ መመሪያዎች ላይ ከተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህብረቶች ጋር የመጀመሪያ ዙር ግብዓት የማሰባሰቢያ ውይይት እያካሄደ ይገኛል፡፡ በውይይት መክፈቻ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንዳሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀገራችን የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረግ ይችሉ ዘንድ የህግና ተቋማዊ የሪፎርም ስራዎች ባለፉት ሶስት ዓመታት ሲሰሩ እንደነበረ አንስተው ቀደም ሲል ተጥሎ የነበረውን የህግ ገደብ በአዲሱ አዋጅ ቁጥር 1113/2011 ሙሉ በሙሉ እንዲነሳና ይህን ለማስፈጸም ስልጣን የተሰጠው ተቋሙም ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግ በርካታ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡ ይህን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰላም፣ በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ በልማትና በግጭት አፈታት ጉዳዮች ላይ በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን አይተናል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ህግ ማውጣት በራሱ መልካም ቢሆንም ብቻውን ግን ግብ አይሆንም፡፡ የወጣውን ህግ በአግባቡ ተግበራዊ ማድረግ ካልቻልን ህጉ የሚፈልገውን አላማና ግብ ማሳካት አይችልም ብለዋል፡፡
አቶ ፋሲካው በንግግራቸው አዲሱ ህግ በተሟላ መልኩ ተግባራዊ መሆን እንዲችል በርካታ ህጉን የማስተዋወቅ ስራዎች ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመሆን በስፋት ተሰርቷል ያሉ ሲሆን ዘርፉ በህግና ሰርዓት ይመራ ዘንድ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ተንቀሳቅሰው በመስራት የህብረተሰቡን ችግር መፍታት ይችሉ ዘንድ ለክልሎች ዘርፉን ለመምራት የሚያስችላቸውን ሞዴል አዋጅ አዘጋጅቶ ተልኮላቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም አዋጁን ሙሉ በሙሉ ወደተግባር ለመለወጥ ወደ18 የሚደርሱ መመሪያዎችን አዘጋጅቷል ያሉ ሲሆን በነዚህ መመሪያዎች ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አስተያየት እንዲሰጡባቸው ጥረት ተደርጓል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋለ፡፡ አንዲሁም ዛሬ በመድረኩ የቀረቡት ሰባቱ ረቂቅ መመሪያዎች በጣም መሰረታዊ እንደሆኑ በማንሳት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ጋር በእጅጉ የተያያዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡