በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የእናቶች ቀንን በተለያዩ ዝግጅቶች አስቦ ውሏል፡፡ በመርኃ ግብሩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ የእናቶች ቀንን ስናስብ በእናቶቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ እያሰብን መሆን ይኖርበታል ያሉ ሲሆን በዘፈቀደ ከማክበር ይልቅ የእናቶቻችንን ውለታ እያሰብን እርሱን ለመመለስ መትጋት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሴቶችን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ፤ በሴቶች ላይ የሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲጠናከሩና አቅም እንዲያገኙ በርካታ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የሴቶችን አቅም በማጎልበት ወደ አመራርነት እንዲመጡ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ሴቶችን ዝቅ የሚያደርጉ እሳቤዎችን ማስወገድ፣ ማንኛውንም ነገር ማድረግ እችላለሁ የሚል መንፈስን ማጎልበት ተገቢነው ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተቋሙ የሚሰሩ እናቶች ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥሮላቸው ወጤታማ ስራ እንዲሰሩ ሁሌም ተቋሙ በትጋት እንደሚሰራ ገልጸው የእናቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተቋሙም ሆነ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም የሚመለከታቸው ሁሉ በትጋት ሊሰሩ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዚህ አጋጣሚ የእናቶችን ቀን ስናከብር የእናቶች መብቶቻቸው፣ ጥቅሞቻቸው ተከብረው፣ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው በሀገራቸው እንዲኖሩ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸው ለማሳሰብ እወዳለሁ ያሉ ሲሆን ለእናቶች እንደግለሰብ፣ እንደተቋም፣ እንደሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የእናቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት ጥረት ልናደርግ ይገባል ብለዋል፡፡ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ለፕሮግራሙ መሳካት አስተዋጽዖ ላደረጉ ለማሪ ስቶፕስ ኢንተርናሽናል፣ ሴንተር ፎር አዶለሰንስ ገርልስ ኸልዝ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ማህበር ምስጋናቸውን አቅርበው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ካሁን ቀደም በርካታ ስራዎችን በጋራ ሲሰራ እንደቆየና ወደፊትም እንደሚቀጥል አውስተዋል፡፡