ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፎረም ጋር በመተባበር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ለሚገኙ የመንግስት አካላትና በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በጸደቁ አራት መመሪያዎች ላይ ስልጠና ሰጠ፡፡ ስልጠናው የተሰጠው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የአስተዳደር ወጪ አፈፃፀም መመሪያ ቁጥር 847/2014፣ የሲቪል ማህበረሰብ ፈንድ አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 848/2014፣ የሙያ ማህበራት ድጋፍ እና አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 849/2014 እና የሂሣብ አጣሪዎች፣ የድርጅት ንብረት ግዢ፣ ሽያጭና አወጋገድ ቁጥር 850/2014 በሚሉት መመሪያዎች ላይ ሲሆን የሥልጠናው ተሳታፊዎች በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የክልሉ ባለድርሻ የመንግስት አካላት ናቸው፡፡ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሲቪል ማህበረሰብ ድረጅቶች ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኃይለማሪያም አየለ የስልጠናውን ዓላማ ባስተዋወቁበት ወቅት እንደተናገሩት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አዋጅ ቁጥር 1113/2011ን ለማስፈጸም የሚያስችሉ 4 መመሪያዎች ጸድቀው ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ ወደስራ መግባታቸውን አንስተው መመሪያዎቹ በሚገባ ተግባር ላይ እንዲውሉ ሁሉም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የመንግስት አካላት ተመሳሳይ መረዳት ሊኖር የሚገባ በመሆኑ ይህ ስልጠና ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ 18 መመሪያዎችን ማዘጋጀቱን ያነሱት አቶ ኃይለማሪያም ከነዚህ 18 መመሪያዎች ውስጥ አራቱ በተግባር ላይ ሲገኙ፣ 6ቱ በቅርቡ ጸድቀው ወደተግባር የሚገቡ ሲሆን ቀሪዎቹ 08 መመሪያዎች ላይ ደግሞ በቅርቡ ግብዓት ለመሰብሰብ በሂደት ላይ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ይህ ስልጠና በሁሉም ክልሎች በቅደም ተከተል የሚከናወን እንደሆነ አንስተው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚሰጠው ይህ ስልጠና የመጀመሪያው እንደሆነ አንስተዋል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የልማት አጋር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ረሺድ ሙስጠፋ የቢሮውን መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት የሲቪል ማህበረተሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአራቱ የጸደቁ መመሪያዎች ላይ በሁሉም ክልሎች ሰልጠና ለመስጠት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በክልሉ በመጀመሩ ትልቅ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡ ይህ ስልጠና በክልሉ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮና በፌደራል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እንዲሁም በሲቪል ሶሳይቲ ፎረም ጥረት ብቻ ውጤት የሚያመጣ ባለመሆኑ እዚህ የተገኛችሁ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆናችሁ ድርጅቶች ሁሉ ለአፈጻጸሙ ጥረትና ተሳትፎ ማድረጋችሁ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ ለስልጠናው ዓላማ መሳካትም ሆነ ስራ ላይ እንዲውል ተገቢው ክትትል እንደሚደረግ አንስተው ለባለስልጣን መስሪያቤቱ እና ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፎረም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በስልጠናው ላይ ተሳታፊ የነበሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮች በሰጡት አስተያየት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በክልሉ ይህን ዓይነት መድረክ ማዘጋጀት መቻሉ የሚያስደስት መሆኑን አንስተው በተለይ ቀደም ሲል ከነበረው ስም ተላቆ ወደእኛ መቅረብ በመቻሉ እጅግ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል፡፡ በመመሪዎቹ ላይ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎች ተነስተው በአሰልጣኞቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ቀደም ሲል በሁሉም ክልሎች እየተዘዋወሩ ስልጠናውን ለሚሰጡ ባለሙያዎችና የስራ ኃላፊዎች የአሰልጣኞች ስልጠና የተሰጠ ሲሆን በጸደቁ አራት መመሪያዎች ላይ የሚሰጠው ይህ ስልጠና በሁሉም ክልሎች እንደሚሰጥ ተጠቁሟል፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የተጀመረው ይህ ስልጠና በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ እንድሁም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፎረም አማካኝነት የተዘጋጀ ነው፡፡