ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ፕሮጀክትን ለማስጀመር ከአለም ባንክ እና ከገንዘብ ሚንስቴር ከመጡ ባለሙያዎችና ከተቋሙ ተወካዮች ጋር የትውውቅና የውየይይት መርሃ ግብር አከናውኗል፡፡ በትውውቅ መርኃ ግብሩ ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ባስተላለፉት መልዕክት ባለስልጣኑ ባለፉት ሶስት አመታት ዋና ዋና የሚባሉ የህግና የተቋማዊ ለውጦችን ሲያደርግ ቆይቷል በማለት በተለይም የአዋጁ መሻሻል በህግ በኩል እንዲሁም የተቋሙ ሰራተኞች የአገልጋይነት መንፈስን ተላብሰው ውጤታማ ስራን ይከውኑ ዘንድ ብዙ ስራዎችን ሰርተናል ብለዋል፡፡

ከአለም ባንክና ከገንዘብ ሚንስቴር ጋር ለረጅም ጊዜ ስንነጋገር ቆይተናል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በስሩ በርካታ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የሚመራ እንደመሆኑ ከኛ ጋር ለመስራት መምጣታችሁ እጅግ ደስተኞች ነን እናንተም ትክክለኛው ቦታ መምጣታችሁን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ ብለዋል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለፕሮጀክቱ አዲስ ይሁን እንጂ ማህበራዊ ተጠያቂነትን በተቋሙ ለማረጋገጥ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው ለዚህም ማሳያ ሰባት አባላት ያሉት መማክርት ጉባዔ በተቋሙ መቋቋሙንና ወደተግባር መግባቱን ማሳያ አድርገው አንስተዋል፡፡

በወርልድ ባንክ የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም (social accountability program) ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ በላይ አዲስ በበኩላቸው ማህበራዊ ተጠያቂነት ከተጀመረ ረጅም ጊዜ መሆኑን አንስተው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የማህበራዊ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የመደገፍና የመምራት ኃላፊነት ያለው በመሆኑ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር መስራታችን ለእኛ ትልቅ እድል ነው ብለዋል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ማህበራዊ ተጠያቂነትን እንደመሳሪያ ሊጠቀመው እንደሚችል አውስተው አካሄዱም የሚሆነው በቅድሚያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ምን እንደሆነ ግንዛቤ መፍጠር አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ አቶ ወርቅነህ ደነቀው በገንዘብ ሚኒስቴር የማህበራዊ ተጠያቂነት አማካሪ በበኩላቸው ማህበራዊ ተጠያቂነት በመንግስትና በህዝብ መካከል የሚደረግ መሆኑን አንስተው ባለስልጣኑ ከሲቪል ማህበራት ጋር ቀረቤታ ያለው በመሆኑ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለዚህ አመቺ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡ አያይዘውም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በኩል ያለው ስራ ከፍተኛ ነው ያሉ ሲሆን ለሚሰሩት ስራ ምን ያህል ተጠያቂ ናቸው፤ ውጤታማ የሆነ የህዝብ ተሳትፎ አለወይ እንዲሁም በቀላሉ ምላሽ መስጠት ይቻላል ወይ የሚለውን መከታተል ተገቢ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም (social accountability program) ባለሙያዎች ተመድበው ወደ ተግባር መገባቱን በትውውቅ መርኃ ግብሩ ላይ የተጠቆመ ሲሆን ፕሮግራሙ በገንዘብ ሚንስቴር የሚመራ ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አመራሮችና ሰራተኞች በቀጣይ ተከታታይ ስልጠናዎችን እንደሚወስዱና መሪ እቅድ ተዘጋጅቶ በቀጣዩ ሳምንት ወደተግባር እንደሚገባ በእለቱ ተጠቁሟል፡፡