በምዝገባ ስርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኤ.ፌ.ዲ.ሪ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስም ባስተላለፉት መልዕክት ሁሉም የፍትህ ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ሃላፊዎች እንዲሁም በዚህ ተቋም የሚሰሩ አቃቤ ህጎች ሃብታቸውን፣ንብረታቸውንና ገቢያቸውን የማስመዝገብ ግዴታ አለባቸው በማለት ከዚህ ቀደም በወረቀት የሃብት ማስመዝገብ ስራው ቢሰራም አሁንም ኮሚሽኑ ባዘጋጀው የኦንላይን ምዝገባ መሰረት ግዴታችንን መወጣት እንቀጥላለን ሲሉ ገልጸዋል ፡፡ ሌላው በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የፌደራል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር ክቡር አቶ ወዶ አጦ ባስተላለፉት መልዕክት በሃገር ደረጃ እየተካሄደ ያለውን የስነ-ምግባር ግንባታና የሙስና መከላከል ስራን ተቋማቸው እያስተባበረ እንደሚገኝ በመናገር ይህንንም ሃላፊነት ለመወጣት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በርካታ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን አንስተዋ፡፡
ሙስናን ከመከላከል አኳያ እንደ አንድ መሳርያ ወይም አቅጣጫ ስንጠቀምበት የነበረው የመንግስት ተመራጮችን ፣ተሿሚዎችን እና የሚመለከታቸው ሰራተኞችን ሃብታቸውንና የገቢ ምንጫቸውን እንዲያስመዘግቡ ማድረግ መሆኑን ም/ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው የሃብት አመዘጋገብ ስርዓት በወረቀት የነበረ መሆኑን አስታውሰው የሃብት አመዘጋገብ ስርዓቱን በዘመዊ ዲጂታል አሰራር ቀይረነዋል ብለዋል ፡፡