ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ድርጅት (ኢትዮጵያዊነት ድርጅት) ይፋዊ የማስተዋወቂያ መድረክ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ምሁራን፣ታዋቂ ሰዎችና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ታድመዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባልስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በመድረኩ እንደተናገሩት ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ታሪኮች ባለቤት፤ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ፈርጥ ስትሆን በየወቅቱ ያጋጠሟትን ፈተናዎች በጽናት በመመከት ሉኣላዊነቷን ሳታስደፍር በብዙ ጀግኖች ልጆቿ መስዋዕትነት የኖረች ሀገር ነች ብለዋል፡፡ እንደሃገር በብዙ ፈተናዎች እያለፈን ነው ሲሉ በመግለጽ ነገር ግን አሻጋሪ የሆኑ ሀሳቦች በመኖራቸው ለዚህ ተግባራዊነት ሁሉም አካል ሊተባበር ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ይህንን ሃሳብ ውጤታማ ለማድረግ የተለያዩ አካላት የየራሳቸውን ሚና እንዳላቸው ሁሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በግምባር ቀደምትነት እንደሚጠቀሱ አንስተው አሁን ላይ በልማትና በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የበኩላቸውን ድጋፍ በማበርከት ላይ እንደሚገኙም አብራርተዋል፡፡ አያይዘውም ኢትዮጵያዊነትን ከፍ ለማድረግና በማይናወጥ መሰረት ላይ ለማጽናት ለሚተጋ እንደ ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ያሉ ድርጅቶች አካታች የሆነ ማንም የማይገለልበትና የሁሉም ዜጋ መብት የሚከበርበትን፤ በኢትዮጵያነቱ የሚኮራና ለኢትዮጵያዊት አንገቱን የሚሰጥ ትውልድ ለመፍጠር ጠንክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ተናግረዋ፡፡ በመጨረሻም ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ድርጅት የጀመረውን ክቡር ዓላማ ከግብ ያደርስ ዘንድ እንደ አንድ ባለድርሻ አካል የሚያስፈልገውን ድጋፍ እናደርጋለን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡