የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አመራሮች በአዲስ አበባ በሚገኘው ጀስቲስ ፎርኦል ዋና ቢሮ በመገኘት የስራ እንቅስቃሴውን ተመልክተዋል፡፡ የድርጅቱ መስራችና ፕረዝዳንት ፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴ አጠቃላይ ስለ ድርጅቱ አመሰራረት፣እንቅስቃሴዎችና ስላገኟቸው እውቅናዎች ያስረዱ ሲሆን በዚህ ሂደት ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፋቸውን፣ተስፋ ሳይቆርጡ በትንሽ ነገር ተነስተው አሁን ላይ ውጤታማ ስራ እየሰሩ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡ ድርጅቱ የፍትህ ተቋማትን በአቅም ግንባታ ስራ፣ ግብዓቶችን በሟሟላት፣ በጥናት ላይ የተመሰረተ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት እና በህትመት መልክ በማዘጋጀት ለትውልድ እንዲተላለፍ የሚያደርግ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ እናቶቻቸው ማረሚያ ቤት የሚገኙ 120 ህጻናትን እንደሚደግፍ ገልጸዋል፡፡በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደገለጹት እንደ ሃገር ከዚህ ዘርፍ በርካታ ውጤታማ ተግባር ይጠበቃል ሲሉ በመግለጽ እናንተም በዘርፍ ከተሰማሩ ድርጅቶች ምሳሌ በመሆናችሁ አስከዛሬ ከሰራችሁት በላይ በርካታ ስራ ከናንተ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
አያይዘውም ድርጅቱ ከፕሪዝን ፌሎሽፕ እስከ ጀስቲስ ፎር ኦል ያለው መንገድ ብዙ ውጣ ውረድ ቢኖረውም ጸንቶ በመቆየት ውስጥ ዛሬ የደረሰበትን መመልክት በመቻላችን እንዲሁም እንደ ሃገር ያጣነውን መከባበርና ዝቅ ብሎ ማገልገል እዚህ ተቋም ውስጥ በማየታችን ደስተኞች ነን በማለት ይህንን መልካም ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት በርካታ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እገዛ አንደነበረ ገልጸው ከዚህ መካከል ጀስቲስ ፎር ኦል አንዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡ የፍትህ ሴክተሩን ከመደገፍ አንጻር ትልቅ ስራ እየሰራ ያለ ተቋም እንደሆነ እንረዳለን ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሩ የተጀመረው ሃገራዊ የምክክር መድረክ እንዲሳካ እና ፍትህ ዘርፉን በቀጣይነት እንዲጠናከር የጀመራችሁትን ስራ አጠናክራችሁ እንደምትቀጥሉ እምነቴ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ድርጅቱ ትልቅ አቅም ያለው እንደመሆኑ መጠን የሃገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን መደገፍና መስመር ማስያዝ ይጠበቅባችኋል በማለት በቀጣይም ለሃር በቀል ድርጅቶች ልምድ ማካፈል፤የበጎ ፍቃደኞችን ማሳተፍ እና ዘርፉ ላይ ጥናት ማድረግ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በመጨረሻም ድርጅቱ የመንግስት ተቋማትን ከሚደግፈው በተጨማሪ እኛም ድርጅቱ ምን ላይ ነው ያለው የሚለውን በመመልከት ማገዝ ያስችላል ሲሉ ገልጸዋል፡፡