የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በአራት መመሪያዎች ላይ ከክልል የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለተውጣጡ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ለሁለት ቀናት የሚሰጠውን ስልጠና በዛሬው እለት ጀምሯል፡፡ ስልጠናውን ያስጀመሩት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ አዋጅ ቁጥር 1113/2011 አንደኛው አላማ ጠንካራ፣ ብቁና ውጤታማ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲገነባ በማድረግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ልማትን፣ዴሞክራሲን በአጠቃላይ የህዝብን ጥቅም እንዲያረጋግጡ ማስቻል ነው ያሉ ሲሆን አዋጁ በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆን ከምንሰራቸው በርካታ ስራዎች መካከል አንደኛው አዋጁን ለማስፈፀም የሚያስችል አሰራር መዘርጋት ነው ብለዋል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዘርፉ እንዲጎለብት ከሰራቸው በርካታ ስራዎች መካከል ግልፅ በሆነ አሰራር እንዲመራ በማድረግ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣንም ሆነ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከል በግልፅ የአሰራር ስርዓት የሚመራና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዘርፍ እንዲፈጠር ማድረግ ነው፡፡
 በዚህ መነሻነት መመሪያዎችንና ማንዋሎችን እንዲሁም የአሰራር ሂደቶችን በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ማዘጋጀት አስፈላጊ በመሆኑ ከ18 በላይ መመሪያዎች ተዘጋጅተው ከነዚህ ውስጥ አራቱ ፀድቀው ወደስራ የገቡ መሆኑን በማንሳት ቀሪዎቹ 14 መመሪያዎችም በቅርቡ ለቦርድ ቀርበው የሚፀድቁ ይሆናል ብለዋል ፡፡ ም/ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ከነዚህ መመሪያዎች በተጨማሪ ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘና የተሻለ የክትትልና ግምገማ ማንዋል የተዘጋጀ በመሆኑ ሁሉም ድርጅቶች በአዲሱ የሪፖርት ማንዋል እያቀረቡ ይገኛሉም ብለዋል፡፡

ዘርፉ ወጥ የሆነ አሰራር እንዲከተል እነዚህ ማንዋሎችና መመሪያዎች ትልቅ እገዛ ያደርጋሉ ሲሉ የገለፁት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ይህ መድረክ የተዘጋጀበት ትልቁ ምክንያትም መመሪያዎችን የሚፈፅሙት ክልሎች፣ በክልሎች የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲሁም የባለሥልጣኑ ባለሙያዎች በመሆናቸውና መመሪያዎች መውጣት ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ እንደተናገሩት ይህ የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ ያለው  በመመሪያዎቹ ላይ የጋራ መረዳት እንዲኖርና በምትሄዱበትም ክልል መመሪያው በትክክል ተግባራዊ እንዲሆን የበኩላችሁን እንድትወጡ በማለም ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የአሰልጣኞች ስልጠናው የሚሰጠው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የአስተዳደር ወጪ አፈፃፀም መመሪያ፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ፈንድ አስተዳደር መመሪያ፣ የሙያ ማኅበራት ድጋፍና አስተዳደር መመሪያ እንዲሁም የሂሳብ አጣሪዎች፤ የድርጅት ንብረት ግዢ፣ ሽያጭና አወጋገድ መመሪያዎች ላይ የሚሰጥ ሲሆን በቀጣይ በሁሉም ክልልሎች ስልጠናው ተሰጥቱዋል፡፡