በተቋሙ ለ16ኛ ጊዜ የጸረ-ጾታ ቀን ‹‹ሠላም ይስፈን በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸም ጥቃት ይቁም!›› በሚል መሪ ቃል እንዲሁም ለ16ኛ ጊዜ የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ‹‹ወንድማማችነት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት›› በሚል መሪ ቃል ተከብሯል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደገለጹት ይህንን በዓል ስናከብር ከወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳይ ጋር በማገናኘት ትርጉም ባለው መልኩ ማክበር አለብን በማለት በተለይም በጦርነቱ ጥቃት የደረሰባቸውን ህጻናትና ሴቶች በማሰብ መሆን አለበት ብለዋል፡፡
አያይዘውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር የፈረሱ ከተማዎችን የመገንባት፣በጦርነቱ የአካል እና የሞራል ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖቻችንን የማቋቋም ኃላፊነት አለብን ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አቶ ጂማ ዲልቦ በበኩላቸው በገለጻው ላይ እንዳብራሩት ይህንን በዓል ስናከብር የድል ማግስት በመሆኑ ልዩ እንደሆነ ገልጸው እዚህ ተሰብስበን ይህንን ፕሮግራም ያከበርነው ስለኢትዮጵያ ብለው በየደጀኑ እየሞቱ ባሉ ጀግኖች ወንድም እና እህቶች መሆኑን ማሰብ አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡ መሳቅም ማልቀስም በሃገር ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የብሔር ብሔረሰቦችም ቀን ስናከብር በመሪ ቃሉ እንደተገለጸው በወንድማማችነት መንፈስ በግንባር ድል እንዳደረግን ሁሉ በተቋማችንም እንዲሁም በሁሉም ዘርፍ ውጤት በማስመዝገብ መሆን አለበት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡