የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከፕሮጀስቲስ ሪሰርች ኤንድ ትሬኒንግ ሴንተር ጋር በመተባበር በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ላይ ለተሰማሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተለያዩ ዙሮች በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህግና አስተዳደር ዙሪያ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በስልጠናው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደተናገሩት የቀድሞው አዋጅ ቁጥር 621/2001 በርካታ ክፍተቶች የነበሩበት መሆኑን ጠቁመው በተለይም ድርጅቶች ቦርዱ በወሰነው ውሳኔ ላይ ይግባኝ ብለው ወደ ፍርድ ቤት የማይሄዱበትና የገቢ ምንጫቸው ከውጪ የሆኑ ድርጅቶችንም እንቅስቃሴ በእጅጉ የገደበ ነበር ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም ለውጡ ይዟቸው ከመጣቸው ቱርፋቶች አንዱ ሴክተሩ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ መንቀሳቀስ እንዲችል ገዳቢ እና አሳሪ የነበረውን ህግ ማሻሻልና መለወጥ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ዋና ምክንያትም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሀገር ልማት፣ እድገትና ብልጽግና እንዲሁም ሰላም ትልቅ ሚና ያላቸው በመሆኑና በህገ መንግስቱ የተቀመጠውን የመደራጀት መብት ድንጋጌ ለመፈጸም ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ይሁንና በሀገራችን የታየውን የለውጥ ሂደት ተከትሎ የህግ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ ዜጎች በሰብዓዊና በመልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ ተደራጅተው እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን አንስተዋል፡፡ የተሻሻለውን ህግ በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረገው ሂደት ውስጥ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን የጠቀሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ስልጠናውም የዚሁ አንዱ አካል ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል፡፡ በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ በስልጠናው ለተሳተፉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሰርተፍኬት ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡

የመደራጀት መብት፣ ሰብዓዊነት፣ የህብረተሰቡ የላቀ ተጠቃሚነት!!!

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት!!!