በባለስልጣን መስሪያቤቱ የህወሃት የሽብር ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት የፈጸመበት ቀን “አልረሳውም! እኔም የኢትዮጵያ ሰራዊት ነኝ!” በሚል መሪ ቃል አክብሯል፡፡ መንግስት የህወሃት የሽብር ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት የፈጸመበት ቀን “አልረሳውም! እኔም የኢትዮጵያ ሰራዊት ነኝ!” በሚል መሪ ቃል ታስቦ እንዲውል መወሰኑ ይታወቃል፡: የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በፕሮግራሙ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የዛሬዋ ቀን ሕይወቱን ቀብድ አስይዞ የትግራይን ሕዝብና የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ሲጠብቅ በነበረው የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የተፈጸመውን ታሪክ ይቅር የማይለውን የሕወሃትን የክህደት ተግባር በቁጭት የምናስታውስበት ቀን ነው፡፡ ይህ ድርጊት አስጸያፊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመና በሰው ልጆች ታሪክ በድጋሚ ሊፈጸም የማይችል ክስተት ነው ተብሎ ይገመታል፡፡ የሚጠብቀውን ሰራዊት አዘናግቶ የሚገድል ጤነኛ ህሊና ያለው ሰብዓዊ ፍጡር አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡ የህወሃት ጁንታው ቡድን ግን ይህንን ክህደት በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ያለርህራሄ ፈጽሞታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም አሁንም ይህንኑ የክህደት ተግባሩን በማጠናከር ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር በህዝባችን ላይ መከራና ሰቆቃ በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የህዝባችንን ሰቆቃ ለማስቆምና የሀገራችንን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሁላችንም የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከጁንታው ጋር በማበር በውስጣችን ሆነው መረጃ በማቀበልና አመቺ ጊዜ ፈልገው ጥቃት የሚፈጽሙብንን ጸንተን ያለርህራሄ ልንታገላቸው ይገባል፡፡ የጠላት መሣሪያ የሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንም እየለየን ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ ከአትዮጵያ የምናስቀድመው ምድራዊ ሃይል ሊኖር አይገባምና! ድላችንን እውን እስኪሆን ድረስ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን አሸባሪንና ወራሪውን ጁንታ ልንዋጋው ይገባል፡፡ የምንኖርበትና የምንሠራበትን አካባቢዎች ነቅተን መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ ይህንን ከሃዲ ጁንታ የመዋጋት ኃላፊነት የጥቂቶች ብቻ ሳይሆን የሁላችንም መሆኑን በመገንዘብ መላው የተቋማችን ሰራተኞችና አመራሮች በምንችለው መንገድ ሁሉ ሀገራችንን እንድንታደግና ለመከላከያ ሰራዊታችንና ለመላው የጸጥታ ኃይሎች አስፈላጊን ድጋፍ እንድናደርግ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም በዚሁ አጋጣሚ ድላችንን ለማፋጠን ሲባል በትናትናው ዕለት የወጣውን የአስቸኳያ ጊዜ አዋጅ በማክበርና በማስከበር የበኩላችንን መወጣት እንደሚገባን ለማሳሰብ እወዳለሁ በማለት ገልጸዋል፡፡