የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በባለፉት ሁለት አመታት በርካታ የሪፎርምና የአቅም ግንባታ ስራዎችን ሲሰራ የቆየ መሆኑን ጠቁመው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከተጽዕኖ ነጻ ሆነው የህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ለማድረግ እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡ የባልስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው የባለስልጣኑን የስራ እንቅስቃሴ አብራርተው በተለይ የተቋሙ ስም እንዲታደስና የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ ረገድ በርካታ ስራዎች ተሰርቷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የአዋጁ ለውጥና የተካተቱ መሰረታዊ ጉዳዬች፣የምዝገባ ስርዓቱ ቀላልና ግልጽ መሆኑን፣ስለ ካውንስሉ ምስረታ፣ስለቦርድ አወቃቀር፣ግልጽ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት በርካታ አዲስ መመሪያዎችን ተቋሙ እያዘጋጀ ስለመሆኑ፣ከክልል እና ከፌደራል ባለድርሻ አካላት ጋር እንዴት በቅንጅት እንደሚሰራ እንዲሁም ከአጋር ድርጅቶች ጋር በጋራ ተቋሙ እየሰራ ስለመሆኑ በተለይም CSSP2 የሁልግዜ ተባባሪ ስለመሆኑ ሃላፊዎቹ በገለጻቸው አመላክተዋል፡፡ ፖል ዋልተርስም የቀረበላቸው ገለጻ ግልጽ መሆኑን በማንሳት በቀድሞው አዋጅ ድርጅቶች ሲገጥማቸው የነበረውን ችግር አውቃለሁ አሁን ችግሩ ተቀርፎ ለውጥ በማየቴ ደስተኛ ነኝ ብለዋል፡፡