ለኤጀንሲው የማኔጅመንት አባላት በስነ ምግባር ዙሪያ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
በስልጠናው ላይ የተገኙት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደገለጹት ተቋማችንን ሞዴል ለማድረግ የስነ ምግባር ተምሳሌትና አርበኞች ሆነን መገኘት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ በገለጻው ላይ ‹‹ትኩረት ለትውልድ ለስነምግባር ግንባታ›› በሚል የተገለጸው መልዕክት እንደግለሰብ ሁላችንም የኔ ድርሻ ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ እንድናነሳ ያደርጋል ያሉ ሲሆን ያለማንም ቀስቃሽ ስለ ስነምግባር ማሰብ፣መጠንቀቅ እና ማነጽ ያስፈልጋል ሲሉ አብራርተዋል፡፡ የሆነ ተቋም ወይም ግለሰብ ስለሚቆጣጠረን ሳይሆን በሃላፊነት ስሜት ለሰራተኞቻችን ተከታታይ ስልጠናዎችን በመስጠት በስነምግባር የታነጸ ተቋም መፍጠር ይጠይቀናል ለዚህም ደግሞ ስነ ምግባር ላይ ትኩረት አድርገን እንሰራለን ብለዋል፡፡

የስልጠናው ዓላማ ማሻሻያ ተደርጎበት ስራ ላይ የዋለውን የፌዴራል የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1236/2ዐ13 ለኤጀንሲው አመራሮች ማስተዋወቅ፣የኮሚሽኑን አዋጅ መነሻ በማድረግ እንደ አዲስ የተደራጀውን የስነ-ምግባር መከታተያ ክፍሎች ተጠሪነት፣ የአሰራርና አደረጃጀት ማሳወቅ፣የስነ-ምግባር መከታተያ ክፍል የተቋቋመበትን ዓላማ የኤጀንሲው አመራሮች አውቀውት ቅንጅታዊ አሰራርን ለመዘርጋት፣መከታተያ ክፍሉ ስራውን በሚያከናውንበት ጊዜ በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በገለልተኝነት መርህ መፈፀም እንዲችል ከተቋሙና ከኮሚሽኑ ጋር የሚኖረውን አሰራርና ግንኙነት ግልጽ ማድረግ በማስፈለጉ እንዲሁም ሙስናና ብልሹ አሰራርን መከላከል የአንድ ክፍል ስራ ብቻ ሳይሆን ቅንጅታዊ አስራርና ትብብር የሚጠይቅ በመሆኑ ስልጠናው መዘጋጀቱን ወ/ሮ ትግስት አቡዬ የስነ ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አብራርተዋል፡፡