የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከcivil society fund III እና CSSP II ጋር በመሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ ባዘጋጁት የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ይዘት ጥናት ረቂቅ ሪፖርት ላይ በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ ህብረትና ዓለም ዓቀፍ  ድርጅቶች ተወካዮች እንዲሁም የክልልና የፌዴራል ባለድርሻ አካላት ታድመዋል፡፡

በመርኃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንዳሉት ሀገራችን ምንም እንኳ በበርካታ ውጫዊና ውስጣዊ ጫናዎች ውስጥ ብትሆንም በእውነትና በትጋት በመስራት የሀገራችንን ብልጽግና ለማረጋገጥ በመስራት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም መንግስት የተቋማችንን የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ከፍ ለማድረግ ወደ ባለስልጣን መስሪያ ቤት ያሳደገው በመሆኑ የኢትዮጵያን የሲቪል ማህበረሰብ ዘርፍ እንዲጎለብት ለማስቻልና የጀመራቸውን ስራዎች በበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ዘርፉን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በራስ አቅምና በአጋር አካላት ድጋፍ ጥናት ማድረጉን አንስተዋል፡፡

ይህ አገራዊ የCSO mapping ጥናት በዘርፉ በጥናት ላይ የተመሰረተ መረጃ ለማግኘት እንዲቻልና፣ ተቋማችንም ሆነ በአጠቃላይ የክልል መንግስታት ለሚያከናውኗቸው ስራዎች መነሻና ማጣቀሻ ሆኖ ያገለግላል በማለት ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ እንዲሁም አጋር ድርጅቶች መንግስት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በአገር ልማትና ዴሞክራሲ የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ፤ በዚህ ጥናት የቀረቡ ማጣቀሻዎችን በመጠቀም ለዘርፉ ድጋፍ እንዲያደርጉ የሚያስችላቸው ይሆናል ሲሉ በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ይዘት ጥናት 2013/14 (Ethiopian civil society mapping 2021)   የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ከአውሮፓ ህብረት የሲቪል ሶሳይቲ ፈንድና (CSF III) ከሲቪል ሶሳይቲ ሰፖርት ፕሮግራም (CSSP II) ድጋፍ በዓለም ዓቀፍ አማካሪዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ያዘጋጀው የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት ነው፡፡

በዚህ ጥናት ላይ ሁሉም ክልሎች የተሳተፉ ሲሆን አጠቃላይ የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ዘርፍ ዳሰሳ ጥናት የመጨረሻ ግብዓት የሚሰበሰብበት እንደሆነም ታውቋል፡፡ በጥናቱ ላይ የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች፣ አማካሪዎች እንዲሁም የኤጀንሲው ባለሙያዎች እና የክልል የስራ ሃላፊዎች ተሳትፎ ያደረጉበት እንደሆነም የጥናት ቡድኑ መሪ አቶ ደበበ ኃይለጊዮርጊስ የጥናቱን ይዘት ባብራሩበት ወቅት ገልጸዋል፡፡ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በእለቱ ከኢ.ዜ.አ ጋር በነበራቸው ቆይታ መንግስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በሚመለከት ባደረገው የአዋጅ ማሻሻያ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አንስተው የተቋቋሙለትን ዓላማ ከግብ ማድረስ የሚገባቸው መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ ውጪ ግን የሀገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር ላይ በሚሳተፉና ከዓላማቸው ውጪ በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ላይ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል፤ ወደፊትም አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ካሁን በፊት ሲያደርጋቸው የነበሩ ማጣሪያዎችን ያጠናቀቀ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ በቅርቡ ምርመራውን ይፋ እንደሚያደርግና ይህን መሰረት አድርጎም እርምጃዎችን የሚወስድ እንደሆነ ለኢ.ዜ.አ ተናግረዋል፡፡