“የሚዲያ እና የሲቪል ማህበራት ሚና በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲፈጠር መስራት ወይስ ዴሞክራሲን ማጠናከር?” በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ አቶ ኤርሚያስ በጋሻው እና አቶ ሰለሞን ሙጬ እንዲሁም በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር በአቶ ፋሲካው ሞላ አወያይነት ክርክር አድርገዋል፡፡ በፌደራልም ይሁን በክልል ደረጃ የተዋቀሩ የመንግስት የመገናኛ ብዙኀን የፋይናንስ ነፃነት ስሌላቸው ለፖለቲካ ጫና ተጋልጠዋል ያሉት አቶ ኤርምያስ መገናኛ ብዙኀን ዴሞክራሲ እንዲኖር መስራት እና ለዴሞክራሲ ማደግ አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ መንግሥትን መጠየቅ፣ ተከታትሎ መረጃዎችን ማቅረብ እንዲሁም መብቶች ሲጣሱ ለምን ማለት የመገናኛ ብዙኀን እና የሲቪል ማህበራት ዋነኛ ድርሻ ነው፡፡ ይህ ተግባር በተጠናከረበት ልክ ዴሞክራሲ ማስረፅና መገንባት ይቻላል፡፡ መንግሥትን ወይም ፖለቲካ ፖርቲዎችን ማጠናከር ግን ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

አቶ ሰለሞን በበኩላቸው ዴሞክራሲ ሂደት እንጂ “የሚፈጠር” አይደለም፡፡ የመገናኛ ብዙኀን እና የሲቪል ማኅበራት ተግባር ዴሞክራሲን መፍጠር ሳይሆን ዴሞክራሲን እያጠናከሩ መሄድ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከመንግሥት ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፡፡ ሕገመንግሥቱ እውቅና የሰጣቸው ሰብዓዊ መብቶች እና ሌሎች የሕግ ማዕቀፎች እንዳይጣሱ በመጠበቅ እንዲሁም መንግሥትን ተጠያቂ በማድረግ እና ትክክለኛ መረጃን በመስጠት የመገናኛ ብዙኀን እና የሲቪል ማህበራት ከፍተኛ ሚና አላቸው፡፡ በዚህም ዴሞክራሲን ያጠናክራሉ። ይህ መሬት ላይ በትክክል ይተገበራል ለማለት አስቸጋሪ ቢሆንም በሂደት የሚስተካከል ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

ከ«ሀበጋር»  DEBATES ማኅበራዊ የትስስር ገጽ የተወሰደ፡